የተረሳው የእምቦጭ አረም የጣና ሐይቅ ዙሪያን በድጋሚ መውረሩ ተሰማ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የእምቦጭ አረም በአስፈሪ ሁኔታ የጣና ሐይቅ ዙሪያን በድጋሚ መውረሩን የጣና ሐይቅ እና የሌሎች ውሃ አካላት ልማትና ጥበቃ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ አያሌው ወንዴ (ዶ/ር)÷ ባለፉት ዓመታት የእንቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ በተለያየ መልኩ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ በጊዜያዊነት በሚደረጉ ዘመቻዎች አረሙን በዘላቂነት በማስወገድ የሐይቁን ሕልውና ለመታደግ አላስቻሉም ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይም የእምቦጭ አረም ከወትሮው በተለየና አስፈሪ በሚባል መልኩ በመስፋፋት ሁሉንም የሐይቁን ዙሪያ ዳርቻዎች መውረሩን አስገንዝበዋል፡፡
አረሙ ከዚህ በፊት ከነበረበት መጠን ጨምሮ እስከ ክልሉ መዲና ባሕርዳር ከተማ ባለው የሃይቁ ዙሪያ በመስፋፋት ከፍተኛ ስጋት መደቀኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አብራርተዋል፡፡
አረሙ በጣና ሐይቅ የሚገኙ የዓሣና የጉማሬ ዝርያዎች እንዲጠፉ ከማድረጉ ባለፈ ውሃው በአረሙ እንዲመጠጥ በማድረግ ሐይቁን የሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በተቀመጠው ስትራቴጂያዊ እቅድ ቅድሚያ ሰጥቶ ሃብት በማሰባሰብ በትኩረት አለመስራትና የጸጥታ ችግር ለአረሙ መስፋፋት ቀዳሚ ምክንያት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 24 ሰዓት መስራት የሚችሉ አምስት የእምቦጭ አረም ማስወገጃ ማሽኖች መኖራቸውን ጠቁመው÷ ይሁን እንጂ በበጀት አለመመደብ ምክንያት ሁሉም ሥራ ላይ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ስለሆነም በጣና ሐይቅ ሁሉም ዳርቻዎች በአስፈሪ ሁኔታ እየተስፋፋ ያለውን የእምቦጭ አረም በዘላቂነት ለማስወገድ የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የክልሉ እና የፌዴራል መንግስታት እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ተቋማት፣ ባለሃብቶች፣ ዳያስፖራዎችና የሚመለከታቸው አካላት አረሙን ለማስወገድ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ