የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብርን በሀገሬ መተግበር እፈልጋለሁ – የጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጭነት እየተተገበረ ያለውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር በሀገራቸው መከወን እንደሚፈልጉ የጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ኡሪ ባህ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ኡሪ ባህ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ጋር በሁለትዮሽ እና አኅጉራዊ ጉዳዮች ላይ በአዲስ አበባ በተወያዩበት ወቅት፤ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው አረንጓዴ ዐሻራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህን ውጤታማ መርሐ-ግብርም በሀገራቸው የመተግበር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ልማት በተለያዩ መስኮች ያላትን ልምድ እና ተሞክሮ እያስመዘገበችበት ያለውን ተሞክሮ ወደ ጊኒ መውሰድ እንደሚፈልጉም አስታውቀዋል፡፡
ለዚህም አስፈላጊው የቴክኒክ ድጋፍ እንዲደረግላቸው መጠየቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ከአሁን በፊት በበርካታ መስኮች የተፈራረሟቸውን ስምምነቶች ወደ ተግባር ለማስገባት በትብብር መሥራት እንደሚገባም በውይይቱ ላይ አንስተዋል፡፡
ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ለጊኒ ያላትን ተሞክሮ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ በኢትዮጵያ የውኃ ሃብት ዳግም እንዲያንሠራራ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2020 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጊኒ ያደረጉት ጉብኝት ታሪካዊውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡