Fana: At a Speed of Life!

ከ67 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ በመቀበል የተከሰሱ የአ/አ ገቢዎች ቢሮ ኦዲተሮች ጉዳያቸውን ማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ታዘዘ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ከግብር ከፋዮች ከ67 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ በመቀበል የሙስና ወንጀል የተከሰሱ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኦዲተሮች ማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ሰጠ።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ከባድ ሙስና ወንጀል ክስ እና በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ንብረትን ወይም ገንዘብን ህጋዊ አድርጎ ማቅረብ ወንጀል በየደረጃው ከአንድ ሳምንት በፊት ክስ መስርቶባቸው እንደነበር ይታወሳል።

ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች 1ኛ የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳዳር ገቢዎች ቢሮ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ጽ/ቤት የታክስ ኦዲት ቡድን አስተባባሪ ሃብታሙ ግዲሳ፣ 2ኛ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር ስምረት ገ/እግዚአብሔር፣ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር አቤኔዘር ቶሎሳ፣ ከፍተኛ ግብር ከፋይ የታክስ ኦዲት ከፍተኛ ኦፊሰር ለሚ ሲሌ እና ወ/ሮ መቅደስ ታደለን ጨምሮ በየደረጃው ተሳትፎ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 24 ግለሰቦች ናቸው።

በየደረጃው በቀረበው ክስ ዝርዝር ላይ ከተለያዩ ግብር ከፋይ ደርጅቶች የግብር መጠን እንቀንሳለን፣ እናስቀንሳለን በማለት በጥቅም በመመሳጠር ከተለያዩ ግብር ከፋዮች ከ67 ሚሊየን ብር በላይ ጉቦ በመቀበል ጥቅም ማግኘትና በመንግስት ላይ ጉዳት ማድረስ የሚል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ነው የቀረበው።

በክሱ ላይ በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አድርጎ ማቅረብ ሙስና ወንጀል የተከሰሱ ግለሰቦችም ይገኙበታል።

ከነዚህ ክሱ ከቀረበባቸው ተከሳሾች መካከል 1ኛ፣ 2ኛ፣3ኛ፣ 6ኛ፣ 9ኛ፣ 10ኛ፣ 14ኛ፣ 19ኛ፣ 20ኛ እና 24ኛ ተከሳሾች አጠቃላይ 10 ተከሳሾች የቀረቡ ሲሆን ሌሎች ቀሪ 14 ተከሳሾች ግን ችሎት አልቀረቡም።

ፍርድ ቤቱ በቀረበባቸው ክስ ዋስትና በማያስከለክል ድንጋጌ ስር የተከሰሱ 14ኛ፣ 19ኛ፣ 20ኛ እና 24ኛ ተከሳሾችን ከ10 ሺህ ብር እስከ 100 ሺህ ብር በሚደርስ ዋስትና በማስያዝ ከእስር እንዲፈቱ የፈቀደ ሲሆን ቀሪ ተከሳሾችን ግን የተከሰሱበት ድንጋጌ ዋስትና የሚያስከለክል በመሆኑ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ችሎት ያልቀረቡ ተከሳሾችን ፖሊስ አፈላልጎ እንዲያቀርባቸው ወይም ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ውጤትን ለመጠባበቅ ለሕዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም ቀጥሯል።

በዚህ መዝገብ ላይ በፍትህ ሚኒስቴር የሃብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጀነራል በኩል በተደረገ የኃብት የማጣራት ስራ በተወሰኑ ተከሳሾች ላይ ጉቦ በመቀበል የተገኘ ገንዘብን ተከትሎ የማይንቀሳቀሱ ሶስት የሪል ስቴት እና አንድ ቪላ መኖሪያ ቤቶች በማግኘት ንብረቱ እንዲታገድ መደረጉ ይታወሳል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.