በእሳት አደጋ እናት እና የ6 ወር ልጇ ሕይወታቸው አለፈ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሸገር ከተማ ፉሪ ክፍለ ከተማ ዛሬ በመስሪያና መሸጫ ሼድ ላይ በተከሰተ የእሳት አደጋ አንድ እናት ከ6 ወር ልጇ ጋር ሕይወታቸው አልፏል።
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ እንዳሉት፥
ከንግድ ሱቆቹ መካከል በአንደኛው ነዳጅ በፕላስቲክ ጠርሙስ በችርቻሮ የሚሸጥበት ሱቅ በመሆኑ ለቃጠሎው መከሰትና መባባስ ምክንያት ሆኗል።
የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር 3 የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪና 2 አምቡላንሶች ከ30 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጋር መሠማራታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም አደጋው ወደሌሎች ንግድ ሱቆች ተዛምቶ ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉን ባለሙያው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
ከ6 ወር ልጇ ጋር ሕይወቷ ያለፈችው እናት በእሳት አደጋው ከተቃጠሉት የንግድ ሱቆች ውስጥ በአንደኛው ሱቅ የንግድ ስራ ላይ እንደነበረች ጠቁመዋል።
ከሞቱት በተጨማሪ በአንድ ሰው ላይ ከባድ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፥6 የንግድ ሱቆች መውደማቸውንም ጠቅሰዋል።
በቀጣይ መሰል አደጋ እንዳይከሰት ነዳጅና ተያያዥ ምርቶችን መስፈርቱን ሳያሟሉ በሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ የሚመለከተው አካል ቁጥጥር እንዲያደርግ ተጠይቋል።
በሌላ በኩል አሁን ያለንበት ወቅት ደረቅና ነፋሻማ አየር ያለው በመሆኑ ለእሳት አደጋ መከሰትና መባባስ አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ ዜጎች ተገቢው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አቶ ንጋቱ አሳስበዋል።
በመላኩ ገድፍ