በመዲናዋ ደረጃቸውን የጠበቁ ተርሚናሎች ግንባታ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃቸውን የጠበቁ እና ምቹ ተርሚናሎች ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ገለፀ፡፡
ግንባታቸው ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ የአውቶቡስና የታክሲ ተርሚናሎች መኖራቸውም ተጠቁሟል።
የተርሚናሎቹን ልማት አስመልክቶ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አስመሮም ብርሃኔ እንዳሉት÷ ተጠናቅቀው አገልግሎት ከጀመሩ ተርሚናሎች መካከል ሜክሲኮ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጎን ያለው አንዱ ነው፡፡
ተርሚናሉ በአንድ ጊዜ 15 አውቶቡስና ከ50 በላይ ታክሲዎችን የመያዝ አቅም እንዳለው ገልጸዋል።
ሜክሲኮ ሱዳን ኤምባሲ አካባቢ ያለው እና በአንድ ጊዜ 11 አውቶቡሶችን የመያዝ አቅም ያለው፣ ቄራ አካባቢ (ሰፋ ያለ) ያለው ለ24 መኪናዎች በአንድ ጊዜ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጠት የሚያስችልና 110 ታክሲዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚያስችለው ተርሚናል እና ፓርኪንግ ግንባታ መጠናቀቁን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ሚኒሊየም አዳራሽ አጠገብ ያለው እና በአንድ ጊዜ 30 ታክሲዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ተርሚናል እንዲሁም ወሎ ሰፈር ያለው በአንድ ጊዜ ለ67 መኪናዎች የፓርኪንክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችልና 47 ታክሲዎችን የመያዝ አቅም ያለው ተርሚናልን ወደ አገልግሎት ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል።
ተርሚናሎቹ የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ አስፈላጊው ነገር እንደተሟላላቸው ገልጸው፤ ለአብነትም ሜክሲኮ ሱዳን ኤምባሲ አካባቢ ያለው ተርሚናል ተሳፋሪዎች ትራንፖርት የሚጠብቁበት ማረፊያና መፀዳጃ ቤት መሟላቱን ጠቅሰዋል፡፡
ሜክሲኮ አረቄ ፋብሪካ አካባቢ፣ መገናኛ ቦሌ ክፍለ ከተማ አጠገብ፣ ደጎል አደባባይ አካባቢ፣ ፒያሣ ሚኒሊክ አደባባይ፣ መገናኛ ሙሉጌታ ዘለቀ ህንፃ አካባቢ፣ መገናኛ የካ ክፍለ ከተማ አጠገብ፣ 4 ኪሎ ጆሊ ባር ጀርባ የተለያየ አገልግሎት የሚሰጡ ተርሚናሎች ግንባታ በመካሄድ ላይ እንደሆነ አመልክተዋል።
ተርሚናሎቹ ከመንገድ ዳር ገባ ብሎ ለትራንስፖርት ሰጪውም ሆነ ለትራንስፖርት ተጠቃሚው ምቹ ሆነው የተገነቡ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
አዲስ የተገነቡ እና እየተገነቡ ያሉ ተርሚናሎች ደረጃቸውን የጠበቁ፣ የአካባባውን ገፅታ የሚቀይሩ፣ ምቹ፣ ዘመናዊ እና የትራፊክ መጨናነቅን የሚቀነሱ እንደሆኑም ነው አቶ አስመሮም ብርሃኔ የተናገሩት፡፡
በአጠቃላይም እየለሙ እና ለምተው የተጠናቀቁ ተርሚናሎችና ፓርኪንጎች 37 ያህል እንደሆኑ ገልጸዋል።
በፌቨን ቢሻው