Fana: At a Speed of Life!

ሁሉም አካል አለኝ ያለውን አጀንዳ እንዲያቀርብ እየተሠራ ነው- ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የምክክር ሂደቱ ሁሉንም አሳታፊ ያደረገ እንደመሆኑ ሁሉም አካል አለኝ ያለውን ጥያቄ እንዲያቀርብ እየተሠራ መሆኑን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከ57 ወረዳዎች በኮሚሽኑ የተለዩ የማኅበረሰብ ክፍል ተወካዮች እና ባለድርሻዎች ሲያካሂዱት የነበረው አጀንዳ የማሰባሰብ መርሐ-ግብር ተጠናቅቋል፡፡

የምክክር ሂደቱ ሁሉንም አሳታፊ ያደረገ እንደመሆኑ ሁሉም አካል አለኝ ያለውን ጥያቄ እንዲያቀርብ እየተሠራ መሆኑን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው ተናግረዋል፡፡

በዚህም በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ኃይሎች ጭምር የምክክር ሂደቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ኮሚሽኑ ጥረት ማድረጉን ጠቅሰው÷ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ወገኖችን ለማሳተፍም በበይነ-መረብ (ዙም) ውይይት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ሌላኛው የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ በበኩላቸው÷ በክልሉ የተካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ሐሳብን በነጻነት የማራመድ ልምምድ በተግባር የታየበት እና ስኬታማ እንደሆነ አንስተዋል።

እንዲሁም ከነገ ጀምሮ ለቀጣይ ሦስት ቀናት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ተጽእኖ ፈጣሪና ታዋቂ ግለሰቦችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት የሚሳተፉበት አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባር እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡

በይስማው አደራው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.