Fana: At a Speed of Life!

100 ሺህ ብር ጉቦ ሲቀበል በቁጥጥር ስር ውሏል የተባለ የፌደራል ፖሊስ መርማሪ ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉዞ እግድ አስነሳለሁ በማለት 100 ሺህ ብር ጉቦ ሲቀበል በቁጥጥር ስር ውሏል የተባለው የፌደራል ፖሊስ መርማሪ ላይ ክስ ተመሰረተ።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ ዳዊት ሀይለማሪያም ወልደጊዮርጊስ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 10 ንዑስ ቁጥር (1) እና (2) መተላለፍ በሚል ጉቦ መቀበል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦበታል።

በክሱ ላይ እንደተመላከተው፤ ተከሳሹ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ መምሪያ መርማሪ ሆኖ ሲሰራ የማይገባውን ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ምርመራ እንዲያጣራ ሀላፊነት ተሰጥቶት ከነበረው ላይት ሀውስ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግል/ማህበር ጉዳይ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪ እና በስራቸውም አትሌት የሆኑት 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ከሀገር እንዳይወጡ የተጣለባቸው የጉዞ እግድ ወደ አሜሪካ ለውድድር ለመሄድ እንዲነሳላቸው በመስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት አቤቱታ ሲያቀርቡ የጉዞ እግዱ እንዲነሳ ለማስደረግ በሚል አስተያየት ለፍርድ ቤቱ እንዲቀርብ 800 ሺህ ብር እንዲከፍሉት ጠይቋል።

በዚህም ተከሳሹ የጉዞ እግድ አስነሳለሁ በማለት በመስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት ገደማ በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ገነት ሆቴል ፊት ለፊት ከ1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ተሽከርካሪ ውስጥ 100 ሺህ ብር ተቀብሎ ሲወጣ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የክትትል ባለሙያዎች እጅ ከፍንጅ የተያዘ መሆኑ ተጠቅሶ ጉቦ በመቀበል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦበታል፡፡

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ከክስ ዝርዝሩ ጋር የሰውና የሰነድ ማስረጃን አያይዞ ያቀረበ ሲሆን ተከሳሹም ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ቀርቦ የክስ ዝርዝሩ ከደረሰው በኋላ ከጠበቃ ጋር ተማክሮ ለመቅረብ በይደር ለነገ ተቀጥሯል።

ግለሰቡ በሌላ መዝገብ በተጠረጠረበት የሙስና ወንጀል ጉዳይ የምርመራ ማጣሪያ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.