የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት ፕሮጀክትን ከከተማ ልማቶች ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል – አቶ አሕመድ ሺዴ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት ፕሮጀክትን ከከተማ ልማቶች ጋር ማጣጣም እንደሚያስፈልግ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ አስገነዘቡ፡፡
አቶ አሕመድ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ ከተመራ የቻይና የቴክኒክ ቡድን ልዑክ ጋር በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት ፕሮጀክት ላይ መክረዋል።
የውይይቱ ዓላማ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት ፕሮጀክት ላይ ግምገማ በማድረግ ፕሮጀክቱን ውጤታማ ለማድረግ ምክረ ሐሳብ ማቅረብ መሆኑ ተገልጿል፡፡
አቶ አሕመድ በዚሁ ወቅት መንግሥት ፕሮጀክቱ ቀልጣፋና ውጤታማ ሂደት እንዲኖረው ይፈልጋል ብለዋል።
በተጨማሪም አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት የከተማ ኮሪደር ልማት በማካሄድ ላይ መሆኗን ገልፀው፥ ፕሮጀክቱን ከከተማ ልማቶች ጋር ማጣጣም እንደሚያስፈልግ ማስገንዘባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።
በቻይና ሬልዌይ ኤሪያን ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ኩባንያ የሚመራው የቴክኒክ ቡድንም በቴክኒክ ባለሙያዎች የተደረገውን ጉብኝት አስመልክቶ ሪፖርቱን አቅርቧል።
የፕሮጀክቱን ጉልህ ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት የጥገና ሥርዓቱን ማሻሻል እና ፕሮጀክቱ ከከተማ ልማት ጋር መጣጣም እንዳለበት በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኢትዮጵያ ቴክኒክ ቡድንን በመምራት ከቻይና ባለሙያዎች ቡድን ጋር በመሆን ቴክኒካል ቡድኑ አጠቃላይ ግምገማ እንዲያካሂድና አዋጭ የመፍትሄ ሐሳብ እንዲያቀርብ ተመድቧል።