በ17 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ 35 ሀሰተኛ ካርታ አሰርተው ህጋዊ ለማድረግ በመንቀሳቀስ የተከሰሱ ለብይን ተቀጠሩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት የዋጋ ግምቱ ከ92 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ 17 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ በተለያዩ መጠኖች 35 ሀሰተኛ ካርታ አሰርተው ህጋዊ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ተይዘዋል የተባሉ አምስት ግለሰቦች ላይ የቀረቡ ማስረጃዎችን መርምሮ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ተከሳሾቹ 1ኛ የካርታ እድሳት ክትትል ኦፊሰር ታዳለች ኡርጌ፣ 2ኛ በግል ስራ የሚተዳደረው ሪያድ ሻምሳዲን 3ኛ ፍጹም በፍቃዱ፣ 4ኛ ተሾመ ተሰማ፣ 5ኛ የመሬት ይዞታ ምዝገባ አሰሳ እና የካርታ ስራ ክትትል እና ድጋፍ ባለሙያ ጋሻው ሽፈራዎ ናቸው።
የኦሮሚያ ክልል የፍትህ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ በ1996 የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎች ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 2 (ሀ) እና አንቀጽ 3 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ አቅርቦባቸዋል።
ተከሳሾቹ ለራሳቸው ወይም ለሌላ ሰው ያልተገባ ጥቅም ለማስገኘት በማሰብ በጥቅም በመመሳጠር በቀድሞ በአዲስ አበባ ከተማ በአቃቂ ቃሊቲ ወረዳ 9 ስር የነበረና በአሁን ወቅት በሸገር ከተማ የተከለለ 17 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ በተለያዩ መጠኖች የአካባቢው ነዋሪ ባልሆኑ በ35 ሰዎች ስም የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ በማዘጋጀት የአርሶ አደር ልጆች በሚል የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን ለኮዬ ፌጬ ክ/ከ ማዘጋጃ ቤት የመሬት ፅህፈት ቤት ያስገቡ መሆኑ በክሱ ተጠቅሷል።
በዚህ መልኩ የዋጋ ግምቱ ከ92 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ የግል እና የመንግስት ንብረት ይዞታን በተለያዩ መጠኖች 35 ሰዎችን የአርሶ አደር ልጆች አስመስለው የተዘጋጀ ሀሰተኛ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በመጠቀም በህገ ወጥ መንገድ ይዞታውን ህጋዊ አድርገው ለመሸጥ ሲንቀሳቀሱ ካርታው ሲጣራ ትክክለኛ አለመሆኑና በተጭበረበረ መንገድ የተዘጋጀ እንደሆነ የተደረሰበ መሆኑ ተጠቅሷል።
በሸገር ከተማ በኮዬ ፈጬ ክ/ከ በፕሮጀክት 18 በታህሳስ 18 ቀን 2016 ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ላይ የተጭበረበረ የቤት ባለቤትነት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ፣ በኦሮሚያ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ፣ በገቢዎች ቢሮ ገንዘብ እንደከፈሉ የሚገልጽ ሀሰተኛ የገቢ ደረሰኝ አዘጋጅተው በኮዬ ፈጬ መሬት አስተዳደርና ልማት ቢሮ ይዞታውን ህጋዊ ለማድረግ ደብዳቤ ማስገባታቸውን በክሱ ዝርዝር የጠቀሰው ዐቃቢህግ ተከሳሾቹ በክትትል የተያዙ መሆኑን ገልጾ ሀሰተኛ ሰነዶችን አዘጋጅቶ መጠቀም የሙስና ወንጀል ክስ በየደረጃው አቅርቦባቸዋል።
ተከሳሾቹ በችሎት ክሱ ከደረሳቸውና በዝርዝር ከተሰማ በኋላ የወንጀል ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው፤ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ከ10 በላይ የሰው ምስክሮችን አሰምቷል፤ የሰነድ ማስረጃዎችንም አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱም የተሰሙ ምስክሮችንና ማስረጃዎችን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሕዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጥሯል።
በታሪክ አዱኛ