Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን መካከል የተደረገው የብድር ስምምነት አዋጅ ጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 4ኛ መደበኛ ስብሰባ በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን መካከል የተደረገውን የብድር ስምምነት አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ፡፡

በምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ÷ አዋጁ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያን ጥቅም ባስከበረ መልኩ በሕዝቦች መካካል ያለውን ትስስር ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ እንደሚያስችልም መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

በሀገራቱ መካከል ያለውን ፍላጎት መሰረት ያደረገው የመንገድ መሰረተ ልማት ስምምነቱ÷ ኢትዮጵያን ከደቡብ ሱዳን ጋር ሊያስተሳስር የሚችል ከ738 ሚሊየን 264 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ባልበለጠ ብድር የሚከናወን ነው ብለዋል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ በደቡብ ሱዳን መንገዶች ባለስልጣን እና በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር እንደሚመራም አስታውቀዋል፡፡

ምክር ቤቱ በአዋጁ ላይ ተወያይቶ በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን መካከል የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበውን አዋጅ ቁጥር 1347/2017 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አፅድቋል፡፡

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ የፓሪስ ኢንዱስትሪያዊ ንብረት ኮንቬንሽን ስምምነትን አዋጅ ቁጥር 1351/2017 አድርጎ በአንድ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

እንዲሁም ዓለም አቀፍ ምልክቶችን ከሚመለከተው ከማድሪድ ስምምነት ጋር የተዛመደውን ፕሮቶኮል ለማጽደቅ የቀረበውን አዋጅ ቁጥር 1352/2017 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ለማቋቋም የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ውሳኔ ቁጥር 3/2016 በማድረግ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የፌዴራል የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩትን እንደገና ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለዝርዝር ዕይታ አዋጅ ቁጥር 11/2017 አድርጎ ለሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.