Fana: At a Speed of Life!

ከረሃብ ነጻ ዓለም ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከረሃብ ነጻ ዓለም ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ከተማ በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።

በኮንፈረንሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት እና የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) ዳይሬክተር ጀነራል ገርድ ሙለር ተገኝተዋል።

በተጨማሪም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት እንዲሁም ከ30 ትላልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት የተውጣጡ ከ1 ሺህ 500 በላይ ተሳታፊዎች በኮንፈረንሱ ታድመዋል፡፡

የዩኒዶ ዳይሬክተር ጄነራል ገርድ ሙለር ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ኮንፈረንሱ ለማዘጋጀት የበኩላቸውን ለተወጡ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

በተለያዩ የተፈጥሮ ሃብቶች የበለጸገችው አፍሪካ ያላትን እምቅ ሃብት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸው፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ከረሃብ ነጻ ዓለም ለመፍጠርም ሁሉም ባለድርሻዎች በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

ለዚህም የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ ቴክኖሎጂን እና ሌሎች ዘመኑን የዋጁ ግብዓቶችን መጠቀም እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኮንፈረንሱ ዓለምን ከረሃብ ነጻ በማድረግ ጥረት የተገኙ ውጤቶችና ያጋጠሙ ፈተናዎች ላይ በመምከር ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች እንደሚያስቀምጥ ተመላክቷል፡፡

ኮንፈረንሱ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ ችግርን በዘላቂነት ሊፈቱ የሚችሉ የመፍትሔ ሐሳቦች እንደሚመላከቱም ተገልጿል።

ለሶስት ቀናት የሚካሄደውን ኮንፍረንስ ዩኒዶ፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ መንግስት በጋራ አዘጋጅተውታል።

በመላኩ ገድፍ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.