የኪነት ባለሙያዋን በውጭ ሀገር ለወሲብ ብዝበዛ ያጋለጡ ተከሳሾች በ13 እና በ16 ዓመት እስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሙዚቃ ተወዛዋዥ የሆነችውን ግለሰብን በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ለወሲብ ብዝበዛ አጋልጠዋል የተባሉት ተከሳሾች በ13 እና በ16 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 13ኛ ወንጀል ችሎት ወሰነ።
የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ፍሬህይወት ስለሺ እና አሊ ፈርዳን ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣዉን የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 137 ንዑስ ቁጥር 1 ስር የተመላከተውን፣ በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣዉን አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀፅ 3 4/ እና አንቀፅ 3/2 ስር የተመለከተዉን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ተደራራቢ ክሶችን አቅርቦባቸዋል።
በዚህ በቀረበባቸው በአንደኛ ክስ ላይ እንደተመላከተው 1ኛ ተከሳሽ ካልተያዙ ግብረአበሮች ጋር በመሆን ከኢትዮጵያ የግዛት ክልል ዉጪ ወደ ባህሬን ለስራ መላክ በሚል ሽፋን የዘመናዊ እና ባህላዊ ዘፈን ተወዛዋዥ የሆነችዉን የግል ተበዳይ “ዘመናዊ እና ባህላዊ ዉዝዋዜ እየሰራሽ በየወሩ 500 ዶላር ይከፈልሻል፣ ምግብ እና መኝታ በጥሩ ሁኔታ ታገኛለሽ ትርዒት ስታቀርቢ ትሸለሚያለሽ” በማለት በማታለል ወደ ባህሬን በመውሰድ ቪአይፒ በሚል ቅፅል ስም ከሚታወቅ ግብረአበር ጋር ወሲብ እንድትፈፅም ማድረጋቸው በክስ ዝርዝሩ ላይ ተጠቅሶ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በሰው መነገድ ወንጀል ተከሰዋል።
በ2ኛ ክስ ደግሞ በሁለቱም ተከሳሾች ላይ እንደቀረበው በግል ተበዳይ ግለሰቧ 200 ዶላር ለ1ኛ ተከሳሽ እንዲከፈለው በማድረግ እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ የሚያስተዳድረዉ ሆቴል ውስጥ ግለሰቧ ወደ ሃገሯ እንዳትመለስ የጉዞ ሰነዶቿን በመያዝ ናድያ ለተባለች የአባቷ ስም ለማይታወቅ ግብረአበሩ በማስተላለፍ ግለሰቧ በምታስተዳድረዉ ማርኮፖሎ በተባለ ሆቴል ዉስጥ ለሆቴል አገልግሎት ከሚመጡ ደንበኞቹ ጋር የአልኮል መጠጦችን እንድትጠጣ፤ ዝሙት እና መሰል የወሲብ ተግባራትን እንድትፈፅም ማድረጋቸው በክሱ ተጠቅሷል።
በተለይም በባህሬን መቆየት ከምትችልበት የሶስት ወራት ጊዜ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም እና ቪዛዋ እንዲቃጠል በማድረግ ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ እንድትችል ቪአይፒ በሚል ቅፅል ስም ከሚታወቅ ግብረአበራቸው ጋር ወሲብ እንድትፈፅም ካደረጓት በኋላ ካደረጓት በኋላ በመጋቢት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ ሃገሯ የተመለሰች በመሆኑ ተመላክቶ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በሰዉ መነገድ ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ከሁለቱ ተከሳሾች መካከል አንደኛ ተከሳሽ በቁጥጥር ስር ውላ ክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳት የተደረገ ሲሆን ሁለተኛ ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ ሲታይ ቆይቷል።
ፍርድ ቤቱ በግራ ቀኝ የቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃና ክርክሮችን መርምሮና አመዛዝኖ ተከሳሾችን ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቶ፤ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ 1ኛ ተከሳሽን በ13 ዓመት ጽኑ እስራት 2ኛ ተከሳሽን ደግሞ በ16 ዓመት ጽኑ እስራትና በየደረጃው በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ