Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በወልድያ ከተማ ”ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል፡፡

በኮንፈረንሱ ከወልድያ ከተማና ከሰሜን ወሎ ዞን የመንግሥት ሠራተኞችና የቡድን የሥራ መሪዎች ጋር በወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን እያስከተለ እንደሚገኝ አንስተው፤ ችግሩን ለመፍታት የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በመድረኩ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ ፍስሐ ደሳለኝ በበኩላቸው÷ ሠራተኞች ስለ ሰላም በመምከር የታቀዱ ሥራዎችን ለመፈጸም ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሰላምን ለማረጋገጥ የመንግሥት ሠራተኞች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው÷ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠልና የሕዝቡን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።

በአማራ ክልል ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት እና ወደ ቀደመ ሰላሙ ለመመለስም ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ማቅረባቸውን የከተማው ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.