ኢትዮጵያ ታዳጊ ሀገራት ፍላጎታቸውን ያማከለ ውክልና በተመድ ውስጥ ሊኖራቸው እንደሚገባ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ታዳጊ ሀገራት ፍላጎታቸውን ያማከለ ውክልና በተባበሩት መንግስታት ድርጀት (ተመድ) ውስጥ ሊኖራቸው እንደሚገባ ኢትዮጵያ አስገነዘበች።
ኢትዮጵያ በሩሲያ ካዛን ከተማ የተካሄደውን 16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ውጤት አስመልክቶ ጀኔቫ የሩሲ ፌደሬሽን ቋሚ መልዕክተኛ በተዘጋጀው ማብራሪያ መድረክ ላይ ተሳትፋለች፡፡
በመድረኩ የተሳተፉት በተመድ የጄኔቫ ቢሮ የኢፌዲሪ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጸጋአብ ክበበው እንዳሉት፤ ዓለም አቀፍ ተቋማት የአስተዳደር መዋቅራቸው እንዲሻሻል እርምጃዎች መውሰድ አለባቸው።
በተለይም ታዳጊ ሀገራት በተመድ ውስጥ ፍላጎታቸው ያማከለ ውክልና ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።
ዓለም አቀፍ ግንኙቶች የታዳጊ ሀገራት ድምጽ እንዲሰማባቸው በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
በጄኔቫ የሚገኙ የብሪክስ አባል ሀገራት ቋሚ መልዕክተኞች በሰብኣዊ መብቶች፣ በንግድ፣ በጤና፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የጋራ ዓላማዎችን ለማሳካት በትብብር መስራት እንደሚገባ ገልጸው÷ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በትብር ለመስራት ቁርጠኛ ናት ማለታቸውን በጄኔቭ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡