በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
የውይይት መድረኩ በሁለቱም ክልሎች ባሉ ዩኒቨርስቲዎችበሚከሰቱ ግጭቶች ዙሪያ በመምከር የመፍትሄ ሃሳብ ለመጠቆም ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ከዚህ ባለፈም ውይይቱ በሁለቱ ክልሎች ህዝቦች መካከል ያለውን የእርስ በርስ ግንኙነትና ትስስር ይበልጥ በማጠናከር ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።
እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተቀራርበው በቅንጅት እንዲሰሩ እና የፖለቲካ ዓላማቸውን እና ተግባራቸውን በተለያዩ አካባቢዎች ለደጋፊዎችቻው እንዲያሳውቁ ያስችላል።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሊቀ መንብር አቶ ዳውድ ኢብሳ እና የአማራ ማህበራዊ ራዕይ ሊቀመንር አቶ ስዩም መንገሻ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ወክለው ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፥ የውይይት መድረኩ ፖለቲከኞች ከጥርጣሬ መንፈስ ወጥተው በቅንጅት እና በመግባባት መስራት እንዲችሉ በር የሚከፍት መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሁለቱም ክልሎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚስተዋለውን የተማሪዎች ሞት እና ግጭት ከምንጩ ለማድረቅ የበኩላቸው ድርሻ የሚወጡ መሆኑን አብራርተዋል።
በአዳነች አበበ