የምክክር ኮሚሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብና ውይይት ማካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብና ውይይት ማካሄድ መጀመሩ ተገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፉን በቦንጋ ከተማ ጀምሯል፡፡
በዚህም በክልሉ ከሚገኙ 57 ወረዳዎች በኮሚሽኑ የተለዩ የማህበረሰብ ተወካዮች እና ባለድርሻዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች ፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ መምህራንና አካል ጉዳተኞች በዚህ የአጀንዳ ግብዓት ማሰባሰብ ምዕራፍ ላይ የሚሳተፉ ስለመሆናቸው ተገልጿል፡፡
የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሩ ዘገዬ አስፋው በመክፈቻ ሥነስ-ርዓቱ ወቅት ÷እንደ ሀገር የገጠሙ ችግሮችን በጋራ መፍትሄ ለማስቀመጥ የመድረኩ ተሳታፊዎች የሃሳብ መደማመጥና መከባበርን በተላበሰ መንፈስ ሃላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ በበኩላቸው ÷ ለሀገራዊ ችግሮች ሁሉ በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ ለማስፈን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በአዋጅ መቋቋሙን ጠቁመዋል፡፡
በአጀንዳ ማሰባሰብ መድረኩ የሚሳተፉ ተወካዮች ለኮሚሽኑ የአጀንዳ ቀረጻ ግብዓት የሚሆነውን የግብዓት ሃሳብ እንዲያስረክቡም ኮሚሽኑ አሳስቧል።
ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፈታት በጋራ ቁጭብሎ በመምከር የጸና የጋራ መግባባትእንዲመጣ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ለአጀንዳ ማዋጣቱ የተወከሉ ባለድርሻዎች ቃል ገብተዋል፡፡
በይስማው አደራው