የብረት ኢንዱስትሪ ዘርፉ ለሁለንተናዊ ሀገራዊ ዕድገት ሚናው ከፍተኛ ነው- አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ የሚገኘውን ኤኤምጂ ሆልዲንግስ ጎብኝተዋል።
አቶ መላኩ አለበል በኤኤምጂ ሆልዲንግስ ጉብኝታቸው ከኩባንያው ባለቤት እና አመራሮች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በዚህ ወቅትም የብረት ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው÷ ዘርፉን በአግባቡ ሳይጠቀም በኢኮኖሚ ያደገ ሀገር የለም ብለዋል።
የማምረቻ መሳሪያዎችን በሚፈለገው ልክና መጠን አምርተን ማቅረብ ባለመቻላችን ለዜጎች መፍጠር በሚገባን ልክ የሥራ እድል አልፈጠርንም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ስለሆነም ለአምራቾች የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ስኬትና ችግራቸው ዙሪያ በቅርበት መወያየትና የመፍትሔ አካል መሆን ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ሥራቸውን በውጤታማነትና በዘላቂነት በማስቀጠል ለሀገር እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ መጠየቃቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡