ሠራዊቱ ሰላምን ከማስፈን በተጓዳኝ በልማቱም ውጤታማ ሥራ እያከናወነ ነው – ወ/ሮ አለሚቱ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕግን ከማስከበርና ሰላምን ከማስፈን በተጓዳኝ ለልማት እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።
የጋምቤላ ክልል ከፍተኛ አመራር አባላትና የመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች ሠራዊቱ በክልሉ እያለማ ያለውን የእርሻ ሥራ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ወ/ሮ አለሚቱ በጉብኝቱ ወቅት÷ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ የሚገኝ የሀገር አለኝታ ነው ብለዋል።
ከዚህም ጎን ለጎን በተለያዩ ልማቶች ላይ በመሰማራት የምግብ ዋስትናቸውን በራስ አቅም ለማረጋገጥ አየተካሄደ ባለው ስራም ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን አስታውቀዋል።
በጋምቤላ ክልል ያሉትን የልማት አቅሞች በሙሉ አስተባብሮ ወደ ውጤት ለመለወጥ መንግስት ከሁሉም አካላት ጋር በትብብር ይሰራል ማለታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል፡፡
የመከላከያ መሐንዲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ በበኩላቸው÷ ዋና መምሪያው ለሠራዊቱ መሠረተ ልማቶችን ከማሟላት ባለፈ የሠራዊቱን ሕይወት ለማሻሻል በመላ ሀገሪቱ በግብርና ሥራዎች ላይ መሰማራቱን ተናግረዋል።