Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሹ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሹ ጥንቃቄ በማድረግ በፍጥነት መሰብሰብ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር አሳስቧል፡፡

ሚኒስቴሩ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ÷ እንደ ሀገር በሁሉም አካባቢዎች እየታየ ያለው የሰብል ቁመና የተቀመጠውን ምርትና ምርታማነት እድገት ደረጃ ሊያሳካ በሚችል ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡

የተቀመጠውን ግብ ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት የድህረ-ምርት ብክነትን መቀነስ የሚያስችሉ የቅድመ-ጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተግበር ሰብሉ ያለምንም ብክነት ተሰብስቦ ወደ ጎተራ መግባት እንዳለበት አስታውሷል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየጣለ መሆኑን የጠቆመው ሚኒስቴሩ÷ ዝናቡ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ሳያደርስ በፍጥነት መሰብሰብ እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች የደረሱ ሰብሎችን የተለያዩ ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ማሽነሪዎችን በመጠቀም ምርት እየተሰበሰበ መሆኑን ጠቅሶ÷ ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ቤተሰቦች እና የዘርፉ ባለሙያዎች አርሶ አደሮችን በመደገፍ የደረሱ ሰብሎች ሳይባክኑ እንዲሰበሰቡ ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.