Fana: At a Speed of Life!

ሰዎችን ማሰርና መደብደብን ጨምሮ በተደራራቢ ወንጀሎች የተከሰሱ እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ሰዎችን ያለአግባብ በማሰር፣ በመደብደብ እና ገንዘብ በመቀበል ተደራራቢ ወንጀሎች የተከሰሱ ሰባት ግለሰቦች እድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ወሰነ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በእነ ሰይድ አሚኖ መዝገብ የተካተቱ ሰባት ግለሰቦችን በተጠረጠሩበት የተለያየ የወንጀል ድርጊት በቁጥጥር ስር አውሎ የምርመራ ስራውን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

የፖሊስ የምርመራ ስራ መጠናቀቁን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል የፍትህ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በእነ ሰይድ አሚኖ መዝገብ በተካተቱ ሰባት ግለሰቦች ላይ ባለፈው ዓመት ተደራራቢ ወንጀል ክሶችን አቅርቦባቸው ነበር።

ተከሳሾቹ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቦታዎች በመንቀሳቀስ ‘ደህንነት ነን’ በማለት ከህግ ውጪ ግለሰቦችን በማስፈራራት፣ በማሰር፣ በመደብደብ፣ በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በመቀበል፣ የተለያዩ የሙስና የወንጀል ተግባራትን ሲፈጽሙ እንደነበር ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ የተሳትፎ ደረጃቸውን አመላክቶ ተደራራቢ ክሶችን አቅርቦባቸው ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎች የግራ ቀኝ ክርክሮችን መርምሮና አመዛዝኖ በተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ በመስጠት ተከሳሾቹን ከ5 ዓመት እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.