እቅዶችን ለማሳካት የተለየ የማስፈፀም ስልት መከተል ይገባል – ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሁሉም ዘርፎች የተያዙ እቅዶችን ለማሳካት የተለየ የማስፈፀም ስልት መከተል እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ
የክልሉ መንግስት የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በመድረኩ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ በሁሉም ዘርፎች የተያዙ የተለጠጡ እቅዶችን ለማሳካት የተለየ የማስፈፀም ስልት መከተል ይገባል።
የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብና አሁን እየጣለ ያለውን ዝናብ ተጠቅሞ ተጨማሪ ማልማት ላይ ማተኮር እንደሚገባ አመልክተዋል።
የገቢ አሰባሰብ ስራው የተሻለ ቢሆንም ከበጀት ዓመቱ እቅድ አንፃር በቂ ባለመሆኑ በተቀናጀ አግባብ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
የስራ እድል ፈጠራ የክልሉ መንግስት ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አንስተው፤ በዘርፉ የሚሰሩ ስራዎች ይህን ከግንዛቤ ያስገቡ መሆን እንዳለባቸው መጠቆማቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የመሰረተ ልማት፣ የሰላምና ፀጥታ ዘርፎች በትኩረት እየተሰራባቸው መሆኑን አመላክተው፤ በተለይም በመሰረተ ልማት ዘርፍ የህብረተሰቡ የቅሬታ ምንጭ የሆኑ የገጠር ተደራሽ መንገዶችን ለመስራት በበቂ ዝግጅት ወደ ስራ መግባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።