ፕሮጀክቱ በግብዓት አቅርቦት ችግር እንዳይጓተት እየተሠራ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት የግብዓት አቅርቦቱ የተቀላጠፈ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፍያ ጣቢያዎች ግንባታ ዘርፍ የራስ ኃይል ግንባታ መምሪያ የግዥና ፋይናንስ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ሙሉቀን ዮሴፍ እንደተናገሩት፥ ለፕሮጀክቱ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ወቅቱን ጠብቀው እንዲሟሉ እየተደረገ ነው።
የፕሮጀክቱ የግብዓት አቅርቦት እንዲፋጠን የሥራ ክፍሉ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉ ብረቶችን በጨረታ ገዝቶ አስቀድሞ ማስገባቱንም አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በግዥ ሥርዓቱ ላይ የሚያጋጥመውን መጓተት ለመቅረፍ እንዲሁም ጊዜንና ወጪን ለመቆጠብ በሳይቱ ላይ ጥራት ያለው ብሎኬት በራስ ኃይል መመረቱን ገልጸዋል።
በዚህም ከ50 ሺ በላይ ብሎኬት በማምረት ከሦስት ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ማዳን ተችሏል ብለዋል፡፡
በራስ አቅም ከሚከናወነው ሥራ በተጓዳኝ ከመከላክያ ግንባታ ግብዓቶች ማምረቻ ድርጅት ጋር ስምምነት በመፈጸም የኮንክሪት ሙሌት ሥራ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
ለፕሮጀክቱ አስፈላጊ ግብዓቶችን በወቅቱ ለማቅረብ የሚያስችሉ ሥራዎች ቀድመው በመከናወናቸው እና ሳይት ላይ በመድረሳቸው የፕሮጀክቱ አፈጻጸም የተሻለ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከፕሮጀክቱ ማጠናቀቂያ ሥራዎች ጋር በተያያዘ ከወር በኋላ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ግዢ ለመፈፀም በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝም አመላክተዋል።