ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሰላምና ጸጥታን በሚመለከት ለምክር ቤት አባላት ከሰጡት ማብራሪያ መካከል፡-
👉 በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር ንግግር አለን፤ ንግግር የሌለ እንዳይመስላችሁ፡፡
👉 ንግግር የሚያደርጉትን እና ሰላም የሚፈልጉትን ሰዎች እንዴት ትነጋገራለህ ከዚህ መንግስት ጋር ብለው የሚወቅሱ ሰዎች ደግሞ አሉ፤ በዚህ ጊዜ ሰላም ፈላጊዎቹ ይደበቃሉ እንጂ ንግግር የለም ማለት አደለም፡፡
👉 በራችን ለሠላም ክፍት ነው፡፡ እኛ የምንፈልገው ሰላም ነው፤ አንድ ወንድም ገድለን ምን እናገኛለን፤ በዚያ መንገድ ማንም እንደማያሸንፈን እናውቃለን፡፡
👉 እኛ ከማንም በላይ ሰላም እንፈልጋለን፤ በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት በልጅነት ወራት ክላሽ ተሸክመን ስለኖርን ክላሽ መሸከም ምን ያህል ጉዳት እንዳለው ይገባናል፡፡
👉 ጦርነትን በተግባር እናውቀዋለን፤ ብዙዎችን ቀጥፎብናል አንፈልገውም፡፡ ሁለተኛ ህልም አለን በዚህ ሀገር ላይ የሚጨበጥ ለውጥ ማምጣት እንፈልጋለን፡፡ ያን ለማድረግ ደግሞ ሰላም በእጅጉ ያስፈልጋል፤ ሰላም በተሟላ ሁኔታ ማረጋገጥ ካልተቻለ የምናስበውን እድገት ማምጣት እንቸገራለን፡፡
👉 ብንገዳደል ምን ያደርግልናል፤ ምን ፋይዳ አለው አይጠቅመንም፤ የሚያስፈልገው ሰላም ነው፡፡
👉 ወደ ኋላ መለስ ብሎ ማየት ጥሩ ነው፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ባለፉት 70 እና 60 ዓመታት ፓርቲ የሚባል እሳቤ የተዋወቅንበት፣ ርዕዮተ-ዓለም የሚባል ንትርክ የጀመርንበት፣ የድጋፍም ይሁን የተቃውሞ ሰልፍ የሚባል ነገር የጀመርንበት ነው፡፡
👉 የፖለቲካ ንትርክ፣ በኅቡዕ መደራጀት፣ የውሸት ፕሮፓጋንዳ፣ ማጠልሸት የተማርንባቸው ዘመናት ናቸው፤ከዚያ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ሽፍታ ነበረ፤ ሽፍታን በአዲስ መንገድ ስሙን አሻሽለን የትጥቅ ትግል ብለን ደግሞ የጀመርነው 50 ወይም 60 ዓመት ይሆናል፡፡
👉 ጥቂት ሽፍቶች በተሰባሰበ ሽፍታ ታጋዮች ተብለው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ዓመታት ከየቦታው ከየአቅጣጫው አለ፡፡ ይህ ጉዳይ በብዙ መንገድ ጉዳት አምጥቷል፡፡
👉 የሚታገለው ሀገር ለማስተዳደርና መንግስት ለመሆን አይመስልም፤ ከፍተኛ የጥላቻ ስሜት አለ፡፡ ይህ አይጠቅምም፡፡