Fana: At a Speed of Life!

በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ 72 ትላልቅ ፋብሪካዎች ሥራ ይጀምራሉ – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ 72 ትላልቅ ፋብሪካዎች ሥራ እንደሚጀምሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የኢንዱስትሪ ዘርፍን በሚመለከት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ÷በዘርፉ በተያዘው በጀት ዓመት 12 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ማኑፋክቸሪንግ ላይ 12 በመቶ እድገት እንደሚጠበቅ ጠቅሰው÷ኮንስትራክሽን ላይ ደግሞ 12 ነጥብ 3 በመቶ ገደማ እድገት ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢንዱስትሪ በዚህ ዓመት ከፍተኛ እድገት እንደሚያመጣ የተጠበቀበት ዋናው ምክንያትም ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ታምርት በሚል ንቅናቄ የጀመርነው ሥራ የሚጨበጥ ፍሬ እንደሚያመጣ ስለሚጠበቅ ነው ብለዋል፡፡

እንዲሁም ኢንዱስትሪን ባለፈው ዓመትና በዚህ ዓመት መጀመሪያ በእቅድ ደረጃ እያንዳንዱ ፋብሪካ ምን ችግር እንዳለው፤ ምን ብናግዘው ምርታማነቱ እንደሚያድግ በጋራ ለመስራት ጥረት ተደርጓልም ነው ያሉት፡፡

ከፋብሪካዎች ጋር የሚያያዝ መብራት ከሞላ ጎደል ተፈትቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ከቴሌና ከባንክ ጋር የሚያያዝ ችግርም ከሞላ ጎደል መፈታቱን አንስተዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመትም በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ 72 ትላልቅ ፋብሪካዎች ሥራ ይጀምራሉ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፡፡

በዚህ መሰረትም በጨርቃ ጨርቅ ላይ 9፣ በምግብና መጠጥ 41፣በኮንስትራክሽንና ኬሚካል 4፣ በቴክኖሎጂ 15 ፕሮጀክቶች እዲሁም 3 ሚሊተሪ ፋብሪካዎች ኢንደስትሪዎች በዚህ ዓመት ምርት ይጀምራሉ ብለዋል፡፡

ከመሬት አቅርቦትና ከእኛ አሰራር ጋር የሚያያዙ በርካታ ችግሮች መፍትሔ እያገኙ መጥተዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ተጨማሪ ስራ የሚያስፈልገውና ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ የሚፈልጉት ከጉምሩክ ጋር የሚያያዝ ስራ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በየሻምበል ምህረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.