ምክር ቤቱ ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) በተገኙበት ዛሬ መደበኛ ስብሰባውን ያካሂዳል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2017 (ኤፍ ቢሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ስብስባውን ዛሬ ያካሂዳል።
የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በስብሰባው ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት በሚቀርቡ ጥያቄዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ።
ይህን ተከትሎም ምክር ቤቱ የመንግሥትን አቋም በማዳመጥ የድጋፍ ሞሽኑን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በስብሰባው ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ።