Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሲካሄድ የቆየው የማኅበረሰብ ክፍሎች ምክክር ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የማኅበረሰብ ክፍሎች የምክክር መድረክ ተጠናቀቀ፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተካሄደ በሚገኘው የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ልየታና የምክክር መድረክ ሦስተኛ ቀን ውሎ የማኅበረሰብ ክፍል ተሳታፊዎች በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ ተወካዮቻቸውን መርጠዋል።

በዚሁ መሠረት በአጀንዳ ልየታና በምክክሩ ላይ ሲሳተፉ የነበሩ ከ10 የማኅበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ተሳታፊዎች 80 ተወካዮቻቸውን ዛሬ መርጠዋል።

ተሳታፊዎቹ ለሦስት ቀናት አካታች፣ አሳታፊ እና ውጤታማ የሆነ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እንደፈጸሙም ገልጸዋል፡፡

ዛሬ ከየማኅበረሰብ ክፍሉ የተመረጡት 80 ተወካዮችም ዓርብ ዕለት በሚጀምረው ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከመንግሥት ተወካዮች፣ ከተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ከታዋቂ ሰዎችና ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በሚደረግ ምክክር ላይ ይሳተፋሉ፡፡

ከዓርብ ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በሚኖረው መድረክም ተወካዮቹ  ከየማኅበረሰብ ክፍሎቹ  የሰበሰቧቸውን አጀንዳዎች ጨምሮ ሌሎች በሚነሱ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ሀገራዊ አጀንዳ የመቅረፅና የተመረጡ አጀንዳዎችን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የማሥረከብ ሥራ ያከናውናሉ፡፡

በተጨማሪም ከባለድርሻ አካላት በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች ምርጫ የሚደረግ ይሆናል፡፡

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.