Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በበርካታ ጉዳዮች አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበች ነው- አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት ሥድስት ዓመታት በበርካታ ጉዳዮች አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገቧን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕረዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

አቶ አደም ፋራህ ከቻይና ሕዝባዊ ምክር ቤት ኃላፊ ሊ ሆንግዦንግ ጋር በቤጂንግ ተወያይተዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያና ቻይና በመተማመን እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አቶ አደም አስገንዝበዋል፡፡

ይህ ግንኙነት በየጊዜው እያደገ መምጣቱንና በአሁኑ ወቅትም ቻይና የኢትዮጵያ ቁጥር አንድ የውጭ ኢንቨስትመንት፣ የውጭ የሰው ኃይል እና ኮንትራቶች ምንጭ መሆኗን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ባላት ግንኙነት የመሰረተ-ልማት ግንባታ፣ አነስተኛ ወለድ ብድር እንዲሁም ኢምፖርትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ መሆኗንም ገልጸዋል፡፡

በርካታ የኢትዮጵያ ምርቶችም በቻይና ገበያ ተቀባይነት እያገኙ መሆኑን በመልካምነት ማንሳታቸውን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በበርካታ ጉዳዮች አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበች መሆኗንም በውይይቱ ላይ አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም የህዳሴ ግድብ ግንባታን 97 ከመቶ መድረሱን፣ ባለፈው ዓመት 8 ነጥብ 1 ከመቶ የኢኮኖሚ እድገት መመዝገቡን፣ በአረንጓዴ ዐሻራ ዘርፍም በሥድስት ዓመታት በርካታ ቢሊየን ችግኞችን መትከል መቻሉን እና ሌሎችም ዋና ዋና ስኬቶችን መመዝገባቸው አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ብሪክስን እንድትቀላቀል የቻይና መንግሥት ላበረከተው አስተዋጽኦም አመስግነዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት የመንግሥት ለመንግሥትና የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሐሳቦችንም አንስተዋል።

በዚህም መሠረት በንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋፋት በትብብር ለመሥራት፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና ሌሎች የመፃዒ ቴክኖሎጂ መስኮች የእውቀት ሽግግርን ማዕከል ያደረገ ትብብር እንዲመሰረት፣ በቡና የተጀመረውን የኢትዮጵያን ምርቶች ወደ ቻይና ኤክስፖርት የማድረግ ሂደት በአይነትም ሆነ በመጠን ለማሳደግ የቻይና መንግሥት አስቻይ ሁኔታዎችን እንዲፈጥር እና ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በቀጣናዊ ፀረ-ሽብር እንቅስቃሴዎችና የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ለመተባበር ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ከወራት በኋላ በሚያደርገው ሁለተኛ ጉባዔ ላይ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

ሊ ሆንግዦንግ በበኩላቸው÷ ቻይና እና ኢትዮጵያ ግንኙነት ከመሰረቱበት ጊዜ ጀምሮ ትብብራቸውን በየጊዜው እያሳደጉ መምጣታቸውን በማውሳት በአሁኑ ወቅት ወደ ላቀ ደረጃ መድረሱን አስታውሰዋል።

በተለይም ወሳኝ በሆኑ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች የጋራ መርህና የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል አድርገው እየሠሩ እንደሆነም ገልጸዋል።

በቀጣይም ከሁለትዮሽ ግንኙነታቸው በተጨማሪ በቻይና አፍሪካ ፎረም፣ በሮድ ኤንድ ቤልት፣ ብሪክስ እና ሌሎች ባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ትብብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በአቶ አደም ፋራህ በኩል የቀረቡ የትብብር መስኮችንም መቀበላቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በዚሁ መሠረት በጋራ ለመሥራትና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማሳደግ መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛው ጉባዔ ላይ እንደሚገኙ አረጋግጠው÷ ጉባዔው የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞታቸው ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.