የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 2 ነጥብ 6 ትሪሊየን መድረሱ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 2 ነጥብ 6 ትሪሊየን መድረሱ ተገለፀ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት ሀገራዊ የሪፎርም እና ዋና ዋና የኢኮኖሚ አፈፃፀም ላይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን÷ በሩብ ዓመቱ በነበረው ሀገራዊ አፈፃፀም ላይ የተዘጋጀ ሪፖርት ቀርቦም ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በዚህም በወጪ ንግድ፣ በመንግስት ገቢ ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲሁም በሌሎችም ዘርፎች የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል።
በአጠቃላይ በ2017 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከባለፈው በጀት ዓመት አንፃር የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት የተመዘገበበት እንደነበር ባሳየው በዚህ ሪፖርት መስከረም 30፣2017 ላይ አጠቃላይ የተቀመማጭ ገንዘብ መጠን 2 ነጥብ 6 ትሪሊየን መድረሱ ተመላክቷል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 121 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ብድር መለቀቁ መገለፁንም የባንኩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በሩብ ዓመቱ አጠቃላይ 640 ሚሊየን የገንዘብ ዝውውር በዲጂታል አማራጮች የተፈፀመ ሲሆን÷ ይህ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የ46 በመቶ እድገት ማሳየቱ ተመላክቷል፡፡
በዲጂታል የክፍያ አማራጮች በነበረው ዝውውርም አጠቃላይ የ3 ነጥብ 1 ትሪሊየን ብር ግብይት መፈፀሙን እና ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ55 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል፡፡
በዚህም በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ በብድር አለቃቀቅ እና አሰባሰብ እንዲሁም በትርፋማነት ረገድ አመርቂ ውጤት መመዝገቡ ተጠቁሟል፡፡