Fana: At a Speed of Life!

በአቶ አደም ፋራህ የተመራው ልዑክ ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የኦርጋናይዜሽን ዲፓርትመንት ጋር የልምድ ልውውጥ አካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ እና በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የተመራ ልዑክ ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የኦርጋናይዜሽን ዲፓርትመንት ጋር የልምድ ልውውጥ አካሂዷል፡፡

አቶ አደም ፋራህ በልምድ ልውውጡ ብልጽግና አዲስ ፓርቲ ቢሆንም በመላ ሀገሪቱ መዋቅር ዘርግቶ የተደራጀ ስራ ለመስራትና የአባላቱን እቅም ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መልካም ውጤት ማስመዝገቡን የተናገሩት አቶ አደም÷በቀጣይ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከ100 ዓመት በላይ ልምድ ካለው ፓርቲ ተሞክሮ ለመቅሰም ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል።

የሲፒሲ ኦርጋናይዜሽን ዲፓርትመንት ምክትል ሚኒስትር ሺ ቺፋንግ በበኩላቸው÷ የሲፒሲ የኦርጋናይዜሽን አሰራር ስርዓት፣ የአሰራር ስርዓት እና አጠቃላይ ሁኔታውን በሚመለከት ተሞክሮዎችን አጋርተዋል፡፡

በዚህም ዲፓርትመንቱ ወደ 100 ሚሊየን የሚጠጉ የሲፒሲ አባላትን ከላይ እስከ ታች ለማደራጀት፣ አቅማቸውን ለማልማትና በቀጣይነት አቅማቸውን ለመገንባት እያደረጋቸው ያሉ ዋና ዋና ስራዎች እንዲሁም እያገኛቸው ያሉ ውጤቶች እና በቀጣይም እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ከላይኛው የፓርቲ መዋቅር እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ያለውን ለመዘርጋት ሃሳብና አቋም የሚሰሩ ስራዎችን አጋርተዋል፡፡

አቶ አደም ፋራህም ብልጽግና ፓርቲ ከአደረጃጀት አንፃር እያከናወናቸው ያሉ ዋና ዋና ጉዳዮችን በውይይቱ አካፍለዋል፡፡

በቀጣይነት በዘርፉ ይበልጥ ትብብር ለማሳደግ በተለይም የአቅም ግንባታና የአባላት ልማት፣ የፓርቲ መዋቅርን ማጠናከር እንዲሁም “በዲጂታል ፓርቲ” ግንባታ መስክ ቴክኖሎጂን አልቆ መጠቀም የሚችል ፓርቲ አንዴት መገንባት ይቻላል በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ አብረው ለመስራትና የበለጠ እየተደጋገፉ ለመቀጠል ጥሪ አቅርበዋል።

የሲፒሲ የዲፓርትመት ሃላፊ በእነዚህ ጉዳዮች ድጋፍ ለማድረግና ትብብራቸውን ለማጠናከር ዝግጁነታቸውን መግለጻቸውን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.