Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፍ የገንዘብ ትብብር ለኢትዮጵያ የልማት ሥራ ድጋፉን እንደሚቀጥል አረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ለሚሠሩ የልማት ሥራዎች የገንዘብ እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ትብብር አስታውቋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ትብብር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማክታሃር ዲዮፕ እና ከሁሉን አቀፍ ኢንቨስትመንት ዋስትና ኤጀንሲ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢትዮጲስ ተፈራ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በምክክሩ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም ከግል ሴክተሮች ጋር በቅርበት መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ በኢኮኖሚ ውስጥ ለማሳተፍ እያደረገች ያለው ጥረትን አቶ አሕመድ አብራርተዋል፡፡

በቅርቡ ለዓለም አቀፍ ኢነቨስተሮች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተደረጉ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በኢኮኖሚው ዘርፍ አዎንታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ጠቅሰው÷ በግሉ ዘርፍም ጥሩ መነቃቃትን መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡

መንግሥት የግሉ ዘርፍ በተለይም በኃይል፣ ማኑፋክቸሪን፣ ቴሌኮም እና ሎጂስቲክስ ዘርፎች ገብቶ ኢንቨስት እንዲያደርግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም ዓለም አቀፍ የገንዘብ ትብብር እና ሁሉን አቀፍ ኢንቨስትመንት ዋስትና ኤጀንሲ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ማክታሃር ዲዮፕ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ለሚሠሩ የልማት ሥራዎች የገንዘብ እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡

ለአዲሱ የአየር መገድ ፕሮጀክት ግንባታ እና ለገጠር ልማት እንዲሁም የግብርና ኢኒሼቲቮችን ለመደገፍ ከአጋር አካላት የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ ፈቃደኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ወገኖች በቅርበት ለመሥራት እና በ 2025 በአዲስ አባባ የሚካሄደውን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስተመንት ዎርክሾፕ በጋራ ለማዘጋጀት ተስማምተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.