Fana: At a Speed of Life!

መድኃኒትን በሀገር ውስጥ ለማምረት የተጀመረው ሥራ አበረታች ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) መድኃኒትን በሀገር ውስጥ ለማምረት የተጀመረው ሥራ አበረታች መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በየዓመቱ ጥቅምት 17 ቀን የሚከናወነው የየም ብሔረሰብ ዓመታዊ ባሕላዊ መድኃኒት ለቀማ ‘ሳሞኤታ’ በፎፋ ወረዳ በቦር ተራራ የፌደራል እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተከናውኗል፡፡

የሀገር በቀል ዕውቀትን ለትውልድ ከማስተላለፍ ባሻገር በግብዓትነት በመጠቀም መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት እየተሠራ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም መድኃኒትን በሀገር ውስጥ ለማምረት የተጀመረው ሥራ አበረታች መሆኑን ገልጸው÷ በዚህም የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርትን ከ8 በመቶ ወደ 36 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው ክልሉ በድንቅ ተፈጥሮ የታደለ መሆኑን ጠቅሰው÷ ተፈጥሮን በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

አካባቢውን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡

የብሔረሰቡን ባሕላዊ የመድኃኒት ለቀማ በተባበሩት መንግሥትታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የየም ዞን አሥተዳዳሪ ሺመልስ እጅጉ ናቸው፡፡

በቀጣይም የባሕላዊ መድኃኒት ለቀማ እና ቅመማን በይበልጥ ለማስፋፋት ትኩረት መሠጠቱን ጠቁመዋል፡፡

በወርቃፈራሁ ያለው እና በርስ ኃይለማርያም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.