Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በብሪክስ ያላት ተሳትፎ ለምጣኔ ኃብታዊ እድገቷ አዎንታዊ ሚና ይጫወታል – አምባሳደር ኤቭጌኒ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2017(ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በብሪክስ ያላት ተሳትፎ ለምጣኔ ኃብታዊ እድገቷ አዎንታዊ ሚና ይጫወታል ሲሉ በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴሬክሂን ተናገሩ።

ከሰሞኑ በሩሲያ ካዛን ከተማ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 16ኛው የብሪክስ ጉባዔ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ምክክር በማድረግ መግባባቶች ላይ በመድረስ መጠናቀቁ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ጥምረቱን ከተቀላቀለች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት በዚሁ ጉባኤ ብሪክስ በቀጣይ ፍትኃዊ የዓለም ሥርዓት ለመፍጠር የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።

በጉባኤው ኢትዮጵያም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ ቡድን የተሳተፈች ሲሆን ፥ የሀገሪቷን ብሔራዊ ጥቅሞች ሊያስጠብቁ የሚችሉ ሃሳቦችን አንጸባርቃለች።

በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይም ያላትን ሚዛናዊ አቋሟን በግልጽ አሳይታላች።

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተሬክሂን በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ ብሪክስ እንደ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፤ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ በቀዳሚነት የጀመሩት ግዙፍ ጥምረት ነው።

እነዚህን ሀገራት ተከትሎ ወደ ጥምረቱ ከተቀላቀሉት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ገልጸው፥ ማዕቀፍ ውስጥ ኢትዮጵያ መካተቷ ለጋራ እድገቷ አስተዋጽዖ ያበረክታል ነው ያሉት።

የብሪክስ አባል ሀገራት በምጣኔ ኃብትና በሕዝብ ለሕዝብ በመሳሰሉ ጉዳዮች በጋራ የሚሰሩ እንደሆነ አንስተው ፥ ይህም የአባል ሀገራት ሁለንተናዊ እድገት ለማሳለጥ የሚያስችላቸው መሆኑን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ኢትዮጵያ በብሪክስ ያላት ተሳትፎ ለራሷ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት የራሱ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ገለጹት አምባሳደሩ ፥ ኢትዮጵያ ለብሪክስ ዓላማ መሳካት የራሷን አስተዋጽኦ እንደምታበረክትም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የብሪክስ አባል ሀገራት የዓለምን አንድ ሦስተኛው ኢኮኖሚና 50 በመቶ የሚጠጋውን የዓለም ሕዝብ የያዙ ሲሆን ፥ አሁን ላይ ከ30 በላይ ሀገራት ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.