Fana: At a Speed of Life!

ቦርዱ 257 ታራሚዎች በይቅርታ እንዲወጡ የውሳኔ ሐሳብ መስጠቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የይቅርታና ምኅረት ቦርድ 257 ታራሚዎች በይቅርታ እንዲወጡ የውሳኔ ሐሳብ መስጠቱን አስታወቀ፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የይቅርታና ምኅረት ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ ዐቃቤ ሕግ ወይኒ ገብረሚካኤል በሰጡት ማብራሪያ÷ ከይቅርታና አመክሮ አፈፃፀም ጋር በተያያዘና የይቅርታ ቦርዱ የውሳኔ ሐሳብ የመስጠትና የማፀደቅ ሥራን አስመልክተው በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራትን አብራርተዋል፡፡

በሰጡት ማብራሪያም ቦርዱ ከፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን እና ከክልል ፍትሕ ቢሮዎች ወይም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጎች የቀረቡ የይቅርታ ጥያቄ የውሳኔ ሐሳብ የተሰጠባቸውን 402 የፌዴራል ታራሚዎች የይቅርታ ጥያቄ መመርመሩን ገልጸዋል፡፡

ከምርመራው በኋላም 257 ታራሚዎች በይቅርታ እንዲወጡ የውሳኔ ሐሳብ በማሳለፍ በኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ፀድቆ ተፈፃሚ ሆኗል ማለታቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

እንዲሁም ቦርዱ የ89 ታራሚዎች የይቅርታ ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን እና 51 ታራሚዎች ደግሞ በቦርዱ ትዕዛዝ የተሰጠባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.