Fana: At a Speed of Life!

አቶ ታዲዮስ ታንቱ በ6 ዓመት ከ3 ወራት ጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥላቻ ንግግር ማሰራጨት እና ግጭት መቀስቀስ ወንጀል የተከሰሱትን አቶ ታዲዮስ ታንቱ በ6 ዓመት ከ3 ወራት ጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የህገ-መንግስትና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት አቶ ታዲዮስ ታንቱን በተከሰሱበትና ጥፋተኝነት በተባሉባቸው 3 ክሶች ነው የጽኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት የጣለባቸው።

አቶ ታዲዮስ ታንቱ ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት እና የእርስ በርስ ግጭት መቀስቀስ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው በፍትህ ሚኒስቴር በተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በኩል ተደራራቢ አራት ክሶች ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል።

ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው አንደኛው ክስ ላይ እንዳመላክተው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/(1)ሀ እና አንቀጽ 257/ሀ ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ግንቦት 11 ቀን እና በመጋቢት 22 ቀን 2014 ዓ.ም እና በተለያዩ የዩቲዩብ ቻናሎች ህዝባዊ አመጽ መቀስቀስ ወንጀል የሚል ነው።

በ2ኛ ክስ በተመለከተ ደግሞ የጥላቻ ንግግርንና ሀሰተኛ መረጃን ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁ 1185/2012 አንቀጽ 4 እና 7/4 በመተላለፍ ታህሳስ 3 ቀን 2014 ዓ.ም በአንድ የዩቲዩብ ቻናል ሀሰተኛ መረጃ አሰራጭተዋል የሚል ክስ በዐቃቤ ሕግ ክስ ቀርቦባቸው ነበር።

በ3ኛ ክስ ደግሞ የወንጀል ህግ ከንቀጽ 32 /1ሀ ና አንቀጽ 337 በመተላለፍ የመከላከያ ሰራዊትን እቅስቃሴን ለማሰናከልና የመከላከል አደጋ እንዲደርስ ለማድረግ በማሰብ ሀሰተኛ ወሬ በመንዛት ቅስቀሳ ማድረግ ወንጀል የተከሰሱ ሲሆን በ4ኛ ክስ የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ ቁ 958/2008 አንቀጽ 14 በመተላለፍ ህዝባዊ አመጽ እንዲፈጠር ቀስቃሽ መልዕክት በድምጽና በተቀሳቃሽ ምስል ተሰራጭቷል የሚል ክስ ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል።

በአጠቃላይ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበባቸው አራት ክሶች ላይ የተጠቀሱትን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ገልጸው፤ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዳሉ ያላቸውን ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቷል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ምስክርን መርምሮ እንዲከላከሉ በሙሉ ድምጽ ብይን መስጠቱ ይታወሳል።

አቶ ታዲዮስ እንዲከላከሉ በተሰጠ ብይን መነሻ የተለያዩ የመከላከያ ምስክሮችን አቅርበው አሰምተው የነበሩ ቢሆንም ባቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ ግን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል (ማስተባበል) አለመቻላቸው ተገልጾ በ3 ክሶች የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየትን ለመጠባበቅ ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም አቶ ታዲዮስ በዚህ እለት የቅጣት ማቅለያ ማቅረብ እንደማይፈልጉና የጥፋተኝነት ፍርዱን እንደማይቀበሉ ለችሎቱ አስታውቀው ነበር።

ይሁንና ፍርድ ቤቱ ግን የ6 ልጆች አባት መሆናቸውንና የ70 ዓመት አዛውንት መሆናቸውን ከግምት ውስጥ አስገብቶ ሁለት የቅጣት ማቅለያ በመያዝ በዕርከን 24 መሰረት በ6 ዓመት ከ3 ወራት ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።

የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ተከሳሹ ላይ የተጣለውን ቅጣት እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ ታሳቢ በማድረግ እንዲያስፈጽም ታዟል።

በታሪክ አዱኛ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.