Fana: At a Speed of Life!

የመከላከያ ሠራዊት ቀን እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 117ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን “በፈተናዎች ውስጥ እየተገነባ የመጣ ሠራዊት” በሚል መሪ ሐሳብ እየተከበረ ነው፡፡

በአከባበሩ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር)፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ፣ የሠራዊቱ አባላት ፣ አባት ዓርበኞች፣ የቀድሞ ሠራዊት አባላት፣ የፌደራል ፖሊስ አባላት፣ የሠራዊቱ ቤተሰቦች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በመስዋዕትነት ያስከበረው መከላከያ ሠራዊት ዘመናዊ ወታደራዊ መዋቅር እና የጦር ሠራዊት ሆኖ ከተዋቀረ ዛሬ 117ኛ ዓመቱን መያዙም በአከባበሩ ላየ ተገልጿል፡፡

ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማስከበርና ማስጠበቅ ባለፈ በተለያዩ የአፍሪካና የእስያ ሀገራት ሰላም በማስከበርና መስዋዕትነት በመክፈል ለሀገራት ሰላም መሆን የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ መቆየቱም ተነስቷል፡፡

ለአብነትም በኮሪያ፣ ኮንጎ፣ ላይቤሪያ፣ ርዋንዳ ፣ ቡሩንዲ፣ ሱዳን ዳርፉር እና በደቡብ ሱዳን አብዬ ግዛት በሰላም ማስከበር ሂደት ከፍተኛ ሚና መጫወቱ ተብራርቷል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የተረጋጋ እንዲሆንና እንደ አልሸባብ ያሉ የሽብር ቡድኖችን በመደምሰስ አኩሪ ገድሎችን መፈጸሙም ነው የተገለጸው፡፡

ሠራዊቱ አሁን ላይ ዘመኑ የደረሰበትን የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ ከመታጠቅ ባለፈ ራሱን በስልጠናና በወትሮ ዝግጁነት ብቁ እያደረገ ማንኛውንም ግዳጅ በብቃት መፈፀም የሚያስችለው ቁመና ላይ እንደሚገኝም በአጽንኦት ተገልጿል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) በአከባበሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ሠራዊታችን በፈተና ውስጥ ያለፈ የማይናወጥና የሀገር መከታ በመሆኑ ሀገርን ከፈተና እየታደገ ነው ብለዋል።

ሠራዊታችንን የሚገጥሙት ፈተናዎች ወደኋላ የሚያስቀሩት ሳይሆኑ ይበልጥ ወደፊት እንዲጓዝ የሚያደርጉትና የሚያጠነክሩት ናቸው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በዓለምሰገድ አሳዬ እና ሶሎሞን ይታየው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.