Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ እየጨመረ ነው – ፕሬዚዳንት ፑቲን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ እየጨመረ እንደሚገኝ አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በካዛን እየተካሄደ ባለው 16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተገናኝተው መክረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር)፤ በሁለትዮሽ መድረካችን ወቅት ላደረግነው ጥልቅ ውይይት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን አመሰግናለሁ ብለዋል።

በሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ቁርኝት ላይ የተመሠረተው የሁለትዮሽ ግንኙነት እያደገ መቀጠሉንም አመላክተው፤ የጋራ የሆነው የብሪክስ መድረክ ሰፋ ላለ የኢኮኖሚ ትብብር እንድንሰራ በር ከፍቶልናል ሲሉ ገልጸዋል።

ሩሲያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ውስጥም ቢሆንም ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬን በማስጠበቅ ረገድ ስኬታማ መሆኗን አድንቀው፤ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን በበኩላቸው፥ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ተቀባይነት እየጨመረ የመጣችው ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት በሁለቱ ሀገራት መካከል በዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖቻችን መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ መሻሻል ታይቶበታልም ብለዋል።

በዚህም ሩሲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ላይ ትኩረት እንደምታደርግ ጠቅሰው፤ በዚህ ዓመት ሩሲያ የመጀመሪያውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ኮንፈረንስ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር እንደምታካሂድ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም፥ የሩስያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊቀመንበር ቫለንቲና ማትቪየንኮ በሚቀጥለው ወር አዲስ አበባን እንደሚጎበኙ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን አክለውም፥ በአሁኑ ወቅት በኢትጵያና ሩሲያ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ እየጨመረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በፋርማሲዩቲካል እና በሌሎች ኢንዱስትሪዎች ያላትን አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗንም ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.