Fana: At a Speed of Life!

ከደንበኛ ሒሳብ ወደ ሌላ ሰው ገንዘብ ያዛወሩ ተከሳሾች እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከባንኩ ደንበኛ ሂሳብ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ወደ ሌላ ግለሰብ አዘዋውረዋል የተባሉ ተከሳሾች እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው።

ተከሳሾቹ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓድዋ ፓርክ ቅርንጫፍ ባንክ ባለሙያ የነበሩት መቅደስ በላይ፣ በዚሁ ባንክ ንኪንግ ኦፊሰር የነበሩት ዮሴፍ ተስፋዬ፣ በዚሁ ባንክ የደንበኞች አገልግሎት መኮንን የነበሩት በፀጋው በቀለ፣ እሱባለው ጎሹ በላይ እንዲሁም አቤኔዘር ተገኔ ናቸው።

የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው ደግሞ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በአራት የንግድ ባንክ ዓድዋ ፓርክ ቅርንጫፍ ሠራተኞች ላይ እና በአንድ ግለሰብ ላይ የሙስና ወንጀል ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1/2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌና እና ከ3 ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር በተጠቀሱ ተከሳሾች ላይ ደግሞ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረትን ወይም ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ መስርቶባቸው ነበር።

በዚሁ መሠረት ከሀገር ውጪ የሚኖሩ አንድ የባንኩ ደንበኛ ሂሳብ ውስጥ ከዕውቅናቸው ውጪ የባንኩን አሰራርና መመሪያ በመተላለፍ በ1ኛ ተከሳሽ እና በ2ኛ ተከሳሾች ግብይት ፈጻሚነት፤ በ3ኛ ተከሳሽ አጽዳቂነት በ2015 ዓ.ም መጨረሻ ሁለት ጊዜ 1 ሚሊየን 800 ሺህ ብር ተቀናሽ በማድረግ ወደ 5ኛ ተከሳሽ የሂሳብ ቁጥር ገቢ መደረጉን ክሱ አመላክቷል፡፡

5ኛ ተከሳሽ ደግሞ በስሙ ወደ ተከፈተ የሂሳብ ቁጥር ከተዘዋወረለት 1 ሚሊየን 800 ሺህ ብር ውስጥ በተለያየ መጠን ለ3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች በሞባይል ባንኪንግ የተላለፈላቸው እና በተለያየ መጠን ገንዘቡ ለግል ጥቅም ውሎ እንደነበርም ተጠቅሷል።

ተከሳሾቹም በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው፥ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሠነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ በአንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 ስር እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ተከላከሉ የሚለውን ብይን ከሰጠ በኋላም ተከሳሾቹ በዋስ ወጥተው የተለያዩ የመከላከያ ማስረጃዎችን አቅርበው ማሰማት ሲጀምሩ 5ኛ ተከሳሽ ግን ችሎት ሳይቀርቡ የዋስትና ግዴታቸውን ሳያከብሩ ቀርተዋል።

ተከሳሾቹ  የመከላከያ ማስረጃ ያቀረቡ ቢሆንም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ግን በተገቢው መከላከል አለመቻላቸው በፍርድ ቤት ተገልጾ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የግራ-ቀኝ የቅጣት አስተያየትን መርምሮ አንድ ተከሳሽ ያቀረቡትን 3 የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ በ2 ዓመት እስራትና በ1 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል፡፡

እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ ያቀረቡትን 4 የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ በ1ዓመት ከ8 ወራት ጽኑ እስራትና በ1 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ሲወስን÷ የ3ኛ ተከሳሽን 6 የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ በ7 ዓመት ጽኑ እስራትና በ 3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በሌላ በኩል 4ኛ ተከሳሽ ያቀረቡትን 5 የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ በ8 ዓመት ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ የተወሰነ ሲሆን፥ 5ኛ ተከሳሽ በሌሉበት በ10 ዓመት ጽኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ በሁሉም ላይ በአንድ ዳኛ የሐሳብ ልዩነት በአብላጫ ድምጽ ተወስኗል።

አንድ ዳኛ የሐሳብ ልዩነት ያቀረቡት 1ኛ ተከሳሽ ከቀረቡባቸው ማስረጃ አንጻር ጥፋተኛ ሊባሉ አይገባም የሚል ሲሆን፥ ሌሎች 3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾችም በክስ ሁለት ጥፋተኛ ሊባሉ አይገባም የሚል እና ገንዘብ የመለሱ ተከሳሽ መኖራቸውን በመጥቀስ ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ በሌሉበት ቅጣት የተጣለባቸው 5ኛ ተከሳሽን የፌደራል ፖሊስ በአድራሻቸው አፈላልጎ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ እና የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤትም በተከሳሾች ላይ የተጣለውን ቅጣት እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.