ጥራት ያለው የዲጂታል ትምህርት ለተማሪዎች ለማድረስ ያለመ ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዲጂታል የትምህርት ስርዓት ላይ ከሚሰራው “ለርኒንግ ሉፕ” ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱ በሁለቱ ተቋማት ትብብር ከፍተኛ ጥራት ያለው የዲጂታል ትምህርት ለኢትዮጵያ ተማሪዎች ለማድረስ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ወቅት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)÷ትምህርት ለጠንካራ እና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ መሰረት ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም ዘርፉን በቀላሉ ሊያግዙ የሚችሉ በቴክኖሎጂ የታገዙ የፈጠራ ስራዎችን የሚሰሩ ሀገር በቀል ተቋማትን መደገፍ ወሳኝ ነው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ምርታማነትን እና ፈጠራን የሚያጎለብት የሰለጠነ የሰው ሃይል በመፍጠር የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን የሚኖረውን ፋይዳም የገለጹ ሲሆን÷ በቴክኖሎጂ የተደገፈ መፍትሄዎችን በማጠናከር መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።
የመማር ተደራሽነትን በዲጂታል መድረኮች ማሳደግ፣ ሀገራዊ የልማት ግቦችን መደገፍ እንዲሁም የሀገሪቱን ስርዓተ ትምህርት የተከተሉ የዲጂታል የመማሪያ መፍትሄዎችን በማዘጋጀት ዘላቂ ዲጂታል ትምህርትን ማሳደግ በስምምነቱ በትኩረት የሚሰሩ ስራዎች ናቸው ተብሏል፡፡
የለርኒንግ ሉፕ መስራችና ስራ አስኪያጂ ኪሩቤል አክሊሉ በበኩላቸው÷ በ2016 የትምህርት ዘመን በዲጂታል መድረኩ ከ260 ሺህ በላይ ተማሪዎች በዲጂታል የቲቶሪያል አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።