Fana: At a Speed of Life!

በቀድሞው የፋይናንስ ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር እነ ቴድሮስ በቀለ ላይ የቅጣት ውሳኔ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በነበሩት እነ ቴድሮስ በቀለ ላይ የቅጣት ውሳኔ ተሰጠ።

የቅጣት ውሳኔውን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹ ÷ 1ኛ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ቴድሮስ በቀለ፣ 2ኛ የቴድሮስ በቀለ ባለቤት ሩት አድማሱ፣ 3ኛ የወ/ሮ ሩት እህት የሆነችው ቤተልሔም አድማሱ እና በግል ስራ ይተዳደራሉ የተባሉት መርሀዊ ምከሰረ ወ/ፃዲቅ፣ ራሄል ብርሀኑ ፣ ፀሐይ ደሜ እና ጌታቸው ደምሴ ናቸው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ አጠቃላይ ሁለት ክሶችን በየተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ ክስ አቅርቦ ነበር።

በ1ኛው ክስ ላይም የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(1) (ሀ) እና (3) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ አቶ ቴድሮስ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሰሩ የተቋሙን አሰራር ባልተከተለ መልኩ አስፈላጊው የደህንነት ይለፍ ያልተደረገለትን የትምህርት ዝግጅቱ ብቁ ያልሆነ በሌላ የሙስና ወንጀል መዝገብ የተከሰሰ አቤል ጌታቸው የተባለ ግለሰብን ከታኅሣስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በተቋሙ የተደራጁና የሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀሎች ፍተሻና ትንተና ከፍተኛ ኤክስፐርት ሆኖ እንዲሰራ ወደ ተቋሙ እንዲቀላቀል አድርገዋል በሚል ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሶ ነበር።

በዚህም ከሰኔ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ አቤል ጌታቸው የተባለውን ግለሰብ የፋይናንስ መረጃ ክትትል እና ቅበላ ቡድን መሪ አድርገው ባልተገባ መንገድ መመደባቸውን በክሱ ተዘርዝሯል።

የተቋሙን የቀደመ የመረጃ ምስጥራዊነት የጠበቀ እና ተጠያቂነትን ያማከለ የመረጃ ቅበላ እና ትንተና አሰራርን በመለወጥ በተቋሙ ውስጥ ስልጣንን ተገን በማድረግ የባለሀብቶችንና የድርጅቶችን የባንክ ሂሳብ አስቀድሞ በማጥናትና መረጃ በመውሰድ በተለያዩ ጊዜያት ለባለሀብቶች ስልክ በመደወል በአካል በማግኘት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲከፍሉ በመጠየቅ የማይከፍሉ ከሆነ ደግሞ የፋይናንስ እንቅስቃሴያቸውን በተመለከተ ምርመራ አድርጎ ለፖሊስ በማስተላለፍ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመርባቸው ይደረግ ነበር በማለት ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል።

አጠቃላይ ተከሳሹ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ውስጥ የነበረውን ኃላፊነት በመጠቀም የፋይናንስ ትንተና በመስራት ውጤቱን ለፍትሕ አካላት የማስተላለፍ ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም ገንዘብ ያላቸው ባለሀብቶችን አሰቀድሞ በማጥናት በመምረጥ በ2013 ዓ.ም እና በ2014 ዓ.ም በተለያዩ ጊዜያት ባለሀብቶችን የባንክ ሒሳባቸው እንደሚታገድ እና በፖሊስ እንደሚመረመሩ እንደሚደረጉ በመግለጽ በማስፈራራት ከ3 ግለሰቦች 3 ሚሊየን 470 ሺህ ብር ገንዘብ ፋፋ ዳባ በተባለ ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገቢ እንዲደረግ በማድረግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ስልጣንን አላግባብ መገልገል ከባድ ሙስና ወንጀል ተከሷል።

በ2ኛው ክስ ደግሞ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን÷ በዚህም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ እና በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አድርጎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 (1) (ሀ) (ለ) እና (ሐ) ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ተከሳሾቹ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ በወንጀል የተገኘ 3 ሚሊየን 470 ሺህ ብር የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቁ የገንዘቡን ምንጭ ለመደበቅ በማሰብ ግብረአበር ነው የተባለ ፋፋ ዳባ እየተባለ የሚጠራ ግለሰብ ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተ ሒሳብ ገቢ እንዲደረግ በማድረግና ከዚሁ ከተጠቀሰው ገንዘብ በተለያዩ መጠን በመጠቀም ሕገ-ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል።

ከ1ኛ እስከ 6 ኛ የተጠቀሱት ተከሳሾች ከጠበቆቻቸው ጋር ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ከተደረገ እና በችሎት ክሱ በንባብ ከተሰማ በኋላ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተው ነበር።

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ከአምስት በላይ ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቶ የነበረ ሲሆን÷ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ቃልን መርምሮ ብይን ሰጥቷል።

በዚህም በ1ኛው ክስ የቀረበባቸው አቶ ቴድሮስ ላይ የተሰሙ ምስክሮች ቃል ተመርምሮ ወንጀሉ መፈጸሙን በምስክር ተረጋግጧል በማለት ፍርድ ቤቱ በ1ኛው ክስ ብቻ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ይከላከሉ የተባሉት በሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 እና በንዑስ ቁጥር 2 ስር ነው።

በ2ኛው ክስ ደግሞ ማለትም በቀረበው በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አድርጎ ማቅረብና መገልገል ወንጀል የተከሰሱት ከ2ኛ እስከ 6ኛ የተጠቀሱት ተከሳሾች የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈጸማቸው በዐቃቤ ሕግ ምስክር የተረጋገጠ መሆኑ ተጠቅሶ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል።

በዚሁ ክስ 7ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሰው ተከሳሽን በሚመለከት በሌለበት ጥፋተኛ የተባለ ሲሆን÷ አቶ ቴድሮስ በቀለ በዚህ ሁለተኛ ክስ የወንጀል ተግባር ስለመፈጸማቸው በሰው ማስረጃ አለመረጋገጡ ተገልጾ ነጻ ተብለዋል።

ተከሳሾቹ በተለያዩ ቀናት የመከላከያ ማስረጃ ያቀረቡ ቢሆንም ባቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ ግን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል አለመቻላቸው ተገልጾ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶባቸዋል።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየቶችን መርምሮ ዛሬ በዋለው ችሎት የቅጣት ውሳኔ ወስኗል።

በዚህም ዐቃቤ ሕግ የወንጀል ድርጊቱ በትብብርና በስምምነት የተፈጸመ መሆኑን ጠቅሶ ያቀረበው የቅጣት አስተያየት በትብብር ስለመፈጸሙ በማስረጃ አስደግፎ አለማቅረቡን የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ ገልጸው የቅጣት ማክበጃውን አለመቀበላቸውን አብራርተዋል።

በዚህም ፍርድ ቤቱ 1ኛ ተከራሽ አቶ ቴድሮስ ያቀረቡት አጠቃላይ 7 የቅጣት ማቅለያ አስተያየት ተይዞላቸው በዕርከን 17 መሰረት በ3 ዓመት ከ3 ወር ጽኑ እስራትና በዕርከን 3 መሰረት ደግሞ በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኗል።

3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ያቀረቡት የቅጣት ማቅለያ ተይዞላቸው እያንዳንዳቸው በዕርከን 22 መሰረት በ5 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራት እና በዕርከን 9 መሰረት በ5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኗል።

በሌለበት ጉዳዩ የታየው 7ኛ ተከሳሽን በሚመለከት የቀደመ የወንጀል ሪከርድ እንዳለበት ማረጋገጫ አለመቅረቡ ተጠቁሞ አንድ ማቅለያ ተይዞለት በዕርከን 26 መሰረት በ7 ዓመት ከ8 ወራት ጽኑ እስራትና በዕርከን 18 መሰረት በ25 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ተጥሏል።

ሌሎች 2ኛ፣ 5ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች ደግሞ ከ7 እስከ 5 የሚደርስ የቅጣት ማቅለያ ተይዞላቸው በዕርከን 22 መሰረት ከ4 ዓመት እስከ 5 ዓመት የሚደርስ የቅጣት ውሳኔ የተጣለባቸው ቢሆንም ተከሳሾቹ ቅጣቱ እንዲገደብላቸው ያቀረቡት አስተያየት ተይዞላቸው ቅጣቱ ተገድቦላቸዋል።

በተጨማሪም የተገደበላቸው ተከሳሾች የ500 የፍርድ ቤት ወጪን እንዲሸፍኑና 2 ሺህ ብር ደግሞ የመተማመኛ ዋስትና እንዲያሲዙ፤ 7ኛ ተከሳሽን ፌደራል ፖሊስ አፈላልጎ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ታዝዟል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.