Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል የወባ በሽታን የመከላከል ተግባር በቅንጅት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገለጸ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በ81 ወረዳዎች የወባ በሽታን የመከላከል ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ ገለጸ።

በቢሮው የወባ በሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ገብረመድህን ክንፉ እንደገለፁት÷ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት የወባ በሽታ ስርጭት የመጨመር አዝማሚያ ታይቷል።

ለበሽታው ስርጭት መጨመር የአካባቢን ንፅህና ያለመጠበቅ እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀስ ቢሆንም፤ የአየር ንብረት ለውጥም የስርጭቱ መንስኤ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችልም አመልክተዋል።

በክልሉ የክረምት ወቅት መውጣትን ተከትሎ የሚከሰተውን የወባ በሽታ ለመከላከል በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመው፤ ይህንንም ለ81 ወረዳዎች በማከፋፈል የወባ መከላከል ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንዲሁም ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ የአልጋ አጎበሮችን ለ37 ወረዳዎች በማሰራጨት ከ2 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች በሽታውን እንዲከላከሉ መደረጉን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በሩብ ዓመቱ የከፋ የወባ በሽታ ስርጭት በሚስተዋልባቸው ስድስት ወረዳዎች በሚገኙ 150 ሺህ መኖሪያ ቤቶች ላይ የወባ ትንኝ መከላከያ ኬሚካል ርጭት መካሄዱን አቶ ገብረመድህን ገልፀዋል።

ለወባ በሽታ ታማሚዎች የሚታደል ከ300 ሺህ በላይ እንክብል ወይም 7 ሺህ ዶዝ መድሃኒት ለወረዳዎቹ ተደራሽ መደረጉንም አስረድተዋል።

በተመሳሳይ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወባ በሽታ ተጋላጭነትን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ ሳሙኤል ዳርጌ ÷ የክረምቱን ወራት መውጣት ተከትሎ የወባ ተጋላጭነት እየጨመረ መምጣቱን ገልፀው ተጋላጭነቱን ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝና በዚህም 1 ነጥብ 2 ሚሊየን የአልጋ አጎበር መሰራጨቱን ጠቁመዋል።

በ31 ወረዳዎች ደግሞ 120 ቀበሌዎችን መሸፈን የሚያስችል የጸረ ትንኝ ኬሚካል ርጭት መካሄዱን ተናግረው ለትንኝ መራቢያነት አመቺ የሆኑ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስ እና የማዳፈን ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.