ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር የኢኮኖሚ አጋርነቷን ለማጠናከር እንደምትሰራ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በተለያዩ መስኮች ያላትን የኢኮኖሚ አጋርነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት ለመስራት ዝግጁ መሆኗን በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ ገለጹ።
አምባሳደር ዳባ ከጃፓን የሩሲያ አምባሳደር ኒኮላይ ስታኒስላቮቪች ኖዝድሬቭን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም አምባሳደር ዳባ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ያላቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ መሆኑን ጠቁመው÷ሀገራቱ በብሪክስ መድረክም በትብብር የመስራት ዕድል መፈጠሩ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በጤና፣ በትምህርት፣ በሳይንስ፣ በግብርና፣ በንግድ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢነርጂ እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ እንደሆነችም ተናግረዋል።
በጃፓን የሩሲያ አምባሳደር ኒኮላይ ስታኒስላቮቪች ኖዝድሬቭ በበኩላቸው÷ብሪክስ ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር መልካም እድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያ እና ሩሲያ የሁለትዮሽ እንዲሁም በብሪክስ ማዕቀፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
አምባሳደሮቹ በቀጣዩ ሳምንት በሩሲያ ካዛን በሚካሄደው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔን አስመልክቶ ሀሳብ መለዋወጣቸውን በጃፓን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።