ኢትዮጵያ የአፍሪካ አኅጉር ሪጅናል የግሎባል ቻይልድ ማዕከል ሆና ተመረጠች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ አኅጉር ሪጅናል የግሎባል ቻይልድ ማዕከል ሆና መመረጧን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የግሎባል ቻይልድ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢና የፕሮጀክቱ ዳይሬክተር ከሆኑት ዚባ ቫግህሪ (ዶ/ር) ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ግሎባል ቻይልድ በሕጻናት መብት እየሠራቸው በነበሩና በቀጣይ በሚሠራቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
በዚሁ ወቅትም ግሎባል ቻይልድ ከካናዳ ውጭ በአምስት አኅጉሮች የግሎባል ቻይልድ ማዕከሎችን ለማቋቋም ሲያስብ÷ በአፍሪካ ኢትዮጵያ የማዕከሉ ዋና መዳረሻ እንድትሆን መምረጡን ሚኒስትሯ አድንቀዋል፡፡
ዚባ ቫግህሪ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ግሎባል ቻይልድ በዋናነት በካናዳ መንግሥት የሚደገፍ መሆኑን አንስተው ለበርካታ ዓመታት በሕጻናት መብት ላይ ሲሠራ መቆየቱን አውስተዋል።
ከአፍሪካ የሕፃናት ፖሊሲ ፎረም ጋር ያለውን ጠንካራ እና ቀጣይነት ያለው ትብብር ግምት ውስጥ በማስገባትም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ግሎባል የሕጻናት ማዕከል ሆና እንድታገለግል መመረጧን ገልጸዋል።