Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከብሪክስ ሀገራት ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች ለመስራት ዝግጁ ናት – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከብሪክስ ሀገራት ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች በስፋት ለመስራት ዝግጁ ናት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሞስኮ እየተካሄደ ባለው የብሪክስ ቢዝነስ ፎረም ላይ በዙም ባደረጉት ንግግር፤ የብሪክስ አባል የሆነችው ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት፣ ንግድና ለኢኮኖሚ ትብብር ምቹ ሀገር መሆኗን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከሌሎች የብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በኢኮኖሚ የመተሳሳር ፍላጎት እንዳላት ጠቅሰው፤ በፍጥነት እያደገ ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለኢንቨስትመንት፣ ለኢኮኖሚ ትብብርና ንግድ ወሳኝ ዕድሎች አሉት ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት እንዳላት ገልጸው፤ በአፍሪካ ሰፊ የገበያ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል አቅምም እንዳላት አስገንዝበዋል።

በአፍሪካ ብሎም በዓለም በመንገደኞችና በጭነት አገልግሎት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርበው የታዳሽ ሃይል እንዲሁም ወጣት፣ የተማረና በቀላሉ ሊሰለጥን የሚችል የሰው ሃይል ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንትና ንግድ ሳቢ የሚያደርጋት አቅም መሆኑን አመልክተዋል።

ኢኮኖሚያችንን ለቢዝነስ ምቹ ለማድረግ በቅርብ ዓመታት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተግብረናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቴሌኮሙኒኬሽንና ፋይናንስን ጨምሮ ቁልፍ ሴክተሮች ላይ በተመለከተ የተደረጉ ለውጦችን በአብነት አንስተዋል።

በቅርቡም የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲመራ የማድረግ ርምጃ መወሰዱን ገልጸው፤ ይህም ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

እነዚህ ማሻሻዎችን ማድረግ ያስፈለገው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆንና ለኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንን ምቹ ሁኔታ የብሪክስ አባል ሀገራት ተጠቅመው በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በታዳሽ ሃይል፣ በማዕድንና በቱሪዝም መስኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የብሪክስ አባል ሀገራት በእነዚህ መስኮች የአፍሪካ መግቢያ በር በሆነችው ኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበት ዕድል ሰፊ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.