ኢትዮጵያ አስተማማኝ የጸጥታና ደኅንነት ተቋም መገንባቷ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የታገዘ ጠንካራና አስተማማኝ የፀጥታና ደኅንነት ተቋም መገንባቷን የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች እና ወታደራዊ አታሼዎች ተናገሩ።
በኢትዮጵያ አስተባባሪነት የተዘጋጀው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ፀጥታና ሰላም” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ከጉባዔው ጎን ለጎንም የመከላከያ ሚኒስትሮቹና አታሼዎቹ የኢትዮጵያ አየር ኃይል እና የመከላከያ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽንን፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደርን፣ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን ጎብኝተዋል።
በዚሁ ወቅትም የኢትዮጵያ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ግንባታ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው÷ በተለይም በሳይበር ደኅንነት፣ በፋይናንስ ደኅንነት፣ በመሰረተ-ልማትና ሌሎች ዘርፎች የላቀ ቴክኖሎጂና የበቁ ባለሙያዎች እንዳሉ ተገንዝበናል ብለዋል።
የዛምቢያ መከላከያ ሚኒስትር፣ በኢትዮጵያ የጋና ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ፣ የዑጋንዳ የመከላከያ ሚኒስቴር የፖለቲካ ዘርፍ ኮሚሽነር÷ ኢትዮጵያ በጸጥታና ደኅንነት፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎትና ሌሎች ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ አሠራሮችን በመዘርጋት ረገድ በአኅጉሪቱ በጥሩ ማሳያነት የሚወሰዱ ተገርባራት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያና ደኅንነት ተቋም ጠንካራ መሰረት ያለው የአፍሪካ ኩራት መሆኑን በጉብኝታችን አረጋግጠናል ሲሉም ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር)÷ ኢትዮጵያ በጸጥታና ደኅንነት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ዘርፎች እያከናወነች ያለውን ተሞክሮ ለአፍሪካውያን ማካፈሏን ጠቅሰዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ የመከላከያ ሚኒስትሮችም የኢትዮጵያን የተቋም ግንባታና ነባራዊ ሁኔታ በማድነቅ በጋራ ለመሥራት ፍላጎት ማሳየታቸውን አንስተዋል፡፡
በአፍሪካዊ የሰላምና ጸጥታ ተቋም ግንባታ ዙሪያ በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ መደረሱንም ነው የገለጹት፡፡
የናይጄሪያ የመከላከያ ሚኒስትር ተወካይ ብርጋዴር ጀነራል ናስር ናጋዳዳ በበኩላቸው÷ ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በመሻት ኢትዮጵያ በመሪነቷ መቀጠሏን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በጸጥታ ዘርፍ ያካበተችው ልምድና የገነባችው ጠንካራ ተቋም አኅጉራዊ ተሳትፎዋን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አንስተው÷ በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የኢትዮጵያ ጠንካራ ተሳትፎና የመሪነት ሚና በይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡