የግብርና ኢኒሼቲቮችን ምርታማነትንና ጥራትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው- አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የግብርና ኢኒሼቲቮችን ከማስተዋወቅ አልፎ ምርታማነትንና ጥራትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በብዛት፣ በፍጥነት እና በጥራት ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ሥራዎችን የማምረት የኢኒሼቲቭ ዓላማችን ተስፋ ሰጪ መንገድ ላይ ነው ብለዋል።
ከእነዚህ ኢኒሼቲቮች መካከል እንደ አኩሪ አተርና ለውዝ የመሳሰሉ የቅባት እህሎች ትኩረት እንዲያገኙ ማስቻሉን ገልጸዋል።
በ2011/12 የምርት ዘመን የአኩሪ አተር ኢንሼቲቭ 14 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በማልማት 252 ሺህ ኩንታል ምርት በማግኘት መጀመሩን አስታውሰው፤ በ2015/16 የምርት ዘመን ከ600 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመሸፈን 11 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።
በ2016/17 ምርት ዘመን ደግሞ ምርታማነትንና ጥራትን ማሳደግ ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቁመዋል።
በለውዝ ኢኒሼቲቭም በ2011/12 የምርት ዘመን በ62 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረው ልማት በ2016/17 የምርት ዘመን 506 ሺህ ሄክታር መሬት መድረስ መቻሉን ጠቅሰው፤ 8 ነጥብ 56 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢኒሼቲቮችን ከማስተዋወቅ በማለፍ ምርታማነትንና ጥራትን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነ አንስተዋል።
በዚህም በቀበሌ አስተዳደር እና የገጠር እድገት ማዕከላት የማሕበረ-ኢኮኖሚ አገልግሎት በመስጠት አርሶ አደሩ የመጀመሪያ ደረጃ ምርቶቹን ወደ ማቀነባበርና እሴት መጨመር ኢኒሼቲቭ ለማሸጋገር እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የአርሶ አደሩን አኗኗር ከመሠረቱ መቀየር እንዲሁም የውጪ ምንዛሬ ገቢያችንን በእጅጉ ማሳደግ እንደ ቀጣዩ ግባችን በማስቀመጥ በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
በዚህ መሠረት አርሶ አደሩ የመዋለ ንዋይ እሳቤዎችን በመረዳት ዝግጅት እንዲያደርግ አስገንዝበው፤ ለዚህ ስኬት ባለድርሻዎችና በየደረጃው ያለ አመራር በከፍተኛ የሕዝብ ወገንተኝነት እንዲንቀሳቀስ አሳስበዋል።