የፓን-አፍሪካ የመከላከያ ኃይሎች ትብብርን እውን የሚያደርግ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግ ተመለከተ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፓን-አፍሪካ የመከላከያ ኃይሎች ትብብርን እውን የሚያደርግ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
የመጀመሪያው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ ከጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በጉባዔው ላይ በአፍሪካ የመከላከያ ኃይሎች መካከል ያለውን ትብብር የተመለከተ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት አምባሳደር ሬድዋን÷ አፍሪካ አንድነቷን ካላጠናከረች ልክ እንደ በፊቱ የሌሎች የመጫወቻ ሜዳ የመሆን ዕጣ ይገጥማታል ብለዋል፡፡
አህጉሪቱ በአሁኑ ወቅት በርካታ ማኅበረ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እየተጋፈጠች ነው በማለት ገልጸው፤ አሸባሪዎች፣ ጽንፈኛ ቡድኖች፣ የባህር ላይ ወንበዴዎችና የድንበር ግጭቶች እያመሷት መሆኑን ገልፀዋል።
የውጭ ኃይሎችም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አህጉራዊ የደኅንነት ስጋት መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።
በመሆኑም አፍሪካ እያጋጠሟት ያሉትን ችግሮች የውጭ ኃይሎች እንዲፈቱ ማማተር እንደማይገባ ጠቁመው÷ ከውጭ የሚመጣ መፍትሔ ቢኖር እርስ በርስ እየተጋጨን ልዩነቶቻችንን አስፍተን በችግር እንድንማቅቅ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ለዚህም የፓን-አፍሪካ የመከላከያ ኃይሎች ትብብርን እውን የሚያደርግ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡
በአፍሪካ የሚከሰቱ አካባቢያዊና ውጫዊ የፀጥታና ደኅንነት ችግሮችን የትኛውም ሀገር ብቻውን እንደማይወጣቸው ጠቅሰው፤ ጠንካራ ፓን-አፍሪካዊ ወታደራዊና የደኅንነት ትብብር ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
አፍሪካውያን ከውጭ በሚገቡ ወታደራዊ መሳሪያዎች ላይ ያላቸውን ጥገኝነት እንዲያላቅቁም የራስን አህጉራዊ አቅም መገንባት ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡