ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የጠፈር ተመራማሪዎች ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ’ ‘ኃላፊነት የተሞላበት የህዋ አጠቃቀም ለዘላቂነት” በሚል መሪ ሃሳብ በጣሊያን እየተካሄደ በሚገኘው 75ኛው ዓለም አቀፍ የጠፈር ተመራማሪዎች ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው።
በጉባዔው ከ 11 ሺህ በላይ የዘርፉ ምሁራን፣ የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም፣ ከአውሮፓ የህዋ ኤጀንሲን ጨምሮ ከመላው ዓለም የተውጣጡ የጠፈር ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል።
በጉባዔው የተሳተፉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) መድረኩ ለኢትዮጵያ የህዋ ፕሮግራም ዓለም አቀፍ አጋሮችን ለማግኘት ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ ኢትዮጵያን በዘርፉ ቀዳሚና ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር እንጠቀምበታለንም ብለዋል።
መድረኩ በትምህርት ዘርፍም ሆነ ኢንዱስትሪ ደረጃ በህዋ ላይ ያሉ አዳዲስ ክስተቶችንና የዘርፉ እድገት ያለበት ደረጃ ሁሉም ሰው እንዲያውቅ ለማድረግ የሚዘጋጅ ነው።
በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች በአንድ መድረክ እንዲገናኙና በጋራ መስራት የሚችሉባቸውን አማራጮች እንዲያዩም ለማስቻል የሚዘጋጅ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡