Fana: At a Speed of Life!

የጀርመን መንግስት ለኢትዮጵያ የ56 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጀርመን መንግስት በኢትጵያ የምግብ ዋስትናን ጨምሮ ለተለያዩ ዘርፎች የሚውል የ56 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

ድጋፉ ይፋ የተደረገው የኢትዮ-ጀርመን የልማት ትብብር መድረክ በአዲሰ አበባ በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡

በመድረኩ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ÷ ኢትዮጵያ ያደረገችውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመተግበር የአጋር አካላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ማሻሻያዎችን በማድረግ በቁርጠኝነት እየተገበረች መሆኗን አስገንዝበው÷ ማሻሻያዎቹን በመተግበር ረገድ እንደ ጀርመን ያሉ አጋር ሀገራት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ጄንስ ሃንፊልድ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያና ጀርመን ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰው÷ የልማት ትብብር መድረኩ የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ያጠናክራል ብለዋል፡፡

በጀርመን ኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስቴር የምስራቅ አፍሪካ ዲቪዥን ኃላፊ ማርከስ ቮን ኤሴን÷ ተቋማቸው ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ የትብብር ዘርፎች ላይ ለመስራት ፈቃደኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ መጨረሻም የጀርመን መንግስት ለምግብ ዋስትና፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ፣ ለትምህርት እና ለመሬት አስተዳደር ማጠናከሪያ የሚውል የ56 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.