ጠቅላይ ፍርድ ቤት እነ ጆን ዳንኤል ላይ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን የዋስትና ብይን አጸና
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከአውሮፕላን አንወርድም በማለት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል ተብለው የተከሰሱት ስድስት ግለሰቦች ላይ በስር ፍርድ ቤት ውድቅ የተደረገባቸውን የዋስትና ጥያቄን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አፀና።
ከ15 ቀናት በፊት በስር ፍርድ ቤት የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ብይን መስጠቱ ይታወሳል።
ዮሃንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል)፣ አማኑኤል መውጫ፣ ናትናኤል ወንድወሰን፣ ኤልያስ ድሪባ፣ ይዲድያ ነጻነት እና እሌኒ ክንፈ የተባሉ ተከሳሾች ግን በጠበቆቻቸው አማካኝነት የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ጠቅሰው ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለው ነበር።
ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ የይግባኝ ባዮችን አቤቱታን እና የከሳሽ ዐቃቤ ሕግ መልስ፣ የግራ ቀኝ ክርክርን መርምሮ የስር ፍርድ ቤት ዋስትና ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉ ከህግ አንጻር ተገቢ ነው በማለት ብይኑን በማጽናቱ ተከሳሾች በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን ይከታተላሉ።
በታሪክ አዱኛ