ጃፓን ለኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ጃፓን ለኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የትግበራ ሂደት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች፡፡
የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ እና ጃፓን በሽግግር ፍትሕ ትግበራ ምዕራፍ ሂደት በጋራ በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
አቶ በላይሁን ይርጋ በዚህ ወቅት÷ በኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እልባት በመስጠት ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ጸድቆ ወደ ትግበራ መግባቱን ገልጸዋል።
አሁን ላይ የፖሊሲው ማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ገልጸው፤ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ላይ የተመላከቱትን ማስተግበሪያ ስልቶች የሚተገብሩ ተቋማትን ለማቋቋም የሕግ ማዕቀፎች በመዘጋጀት ላይ ናቸው ብለዋል።
የጃፓን መንግስት በሕግ ረቂቆቹ ላይ የሚደረጉት የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮችን ጨምሮ በፖሊሲ ትግበራ ፍኖተ ካርታው ላይ የተመላከቱትን ተግባራት በመደገፍ በትብብር እንዲሰራ ጠይቀዋል።
አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ በበኩላቸው÷ ጃፓን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን እድገት እና ልማትን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት እንደምትግፍ ገልጸዋል።
የሽግግር ፍትሕ ሰላምን ለማረጋገጥ እና ዴሞክራሲን ለማስፈን ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሀገራቸው የትግበራ ሂደቱን ለመደገፍ ዝግጁ ናት ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡